በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ ምርጫ እንድታካሂድ ተመድ እና የአፍሪካ ህብረት አሳሰቡ


ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃት እናደርሳለን ብለው እየዛቱ ቢሆንም ሶማሊያ በተደጋጋሚ ያዘገየቻቸውን ምርጫ በዕቅዱ መሰረት እንድታካሂድ የተመድ እና የአፍሪካ ህብረት አሳሰቡ።

ሶማሊያ ብሄራዊ ምርጫን በመጪው ጥቅምት ልታካሂድ አቅዳለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶማሊያ ልዩ ተወካይ ጄምስ ስዋን ለጸጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ገለጻ ላይ "የምርጫው ዝግጅት አልሸባብ እየሰነዘረ ያለውን ዛቻ ታሳቢ ባደረገ መንገድ መከናወን አለበት" ብለዋል።

"አልሸባብ በተለይ በደቡባዊ ምዕራቡ ክፍለ ሃገር የሸብርተኛ ጥቃት እየፈጸመ ነው፥ ታጣቂዎቹን በማሰማራት ሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ማድረሱን እና ማኅበረሰቦችን መክበብን የመሳሰሉ አድራጎቶችን እየፈጸመ ነው" ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ፍራንሲስኮ ማዲየራም በበኩላቸው ለጸጥታ ምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር "የጋራ ትኩረታችን መሆን ያለበት ታጣቂዎች የምርጫ ስርዓቱን እንዳያደናቅፉ መከላከል ነው" ብለዋል።

አልሸባብ በሞቃዲሾም ሆነ በሌሎችም አካባቢዎች ምርጫውን ለማሰናከል የተንኮል አድራጎት በመፈጸም ላይ ነው ያሉት የአህጉራዊው ህብረት ልዩ ተጠሪው ማድየራ ታጣቂው ቡድን ሰዎችን እየጠለፈ፣ በአደባባይ እየረሸነ መሆኑን መዝግበናል ሲሉ አመልክተዋል። በተለይም የማኅበረሰብ አዛውንቶችን በምርጫው እንዳትሳተፉ እያለ ማስፈራራቱ ደግሞ በእጅጉ አሳስቦናል ሲሉም አስታውቀዋል።

ሶማሊያ የሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት የፖለቲካ ተልዕኮ በሀገሪቱ በዚህ የአውሮፓ ዓመት ብቻ 321 ሲቪሎች መገደላቸውን መመዝገቡን ገልጾ አብዛኞቹ የተገደሉት በአልሻባብ ታጣቂዎች እጅ እንደሆነ ተናግሯል።

በሶማሊያ በመንግሥቱ እና በተቃዋሚዎች መካከል ባለው አለመግባባት የተነሳ ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ከየካቲት ወር ጀመሮ በተደጋጋሚ ሲዘገዩ ቆይተዋል።

የሥልጣን ዘመናቸው ከሚፈቅድላቸው ገደብ አልፈው ሥልጣን ላይ ለመቆየት የፈለጉት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ታማኝ ደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል ባለፈው ሚያዝያ ግጭት ተቀሷል፥ ግጭቱ ያቺን ሃገር ወደሌላ የእርስ በርስ ጦርነት አዙሪት እንዳይገፋት አስግቶ እንደነበር አይዘነጋም።

ግንቦት መጨረሻ ላይ በተደረሰ ስምምነት ነው የምርጫ ዕቅድ መንቀሳቀስ የጀመረው።

XS
SM
MD
LG