በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለማቀፍ የረድዔት ሠራተኞች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ ፈቃድ ማግኘቱን ተመድ አስታወቀ


ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ
ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሃያ አምስት ዓለማቀፍ የረድዔት ሰራተኞች ወደ ትግራይ ክልል መግባት እንዲችሉ ፈቃድ መስጠቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ይህን ፈቃድ ማግኘታችን የርዳታ ሰራተኞች ችግሩ በፍጥነት እየተባባሰ ባለበት በትግራይ ክልል ርዳታ ለማድረስ እና ለችግሩ የምንሰጠውን ምላሽ ለማጠናከር መቻላችንን የሚያረጋግጥ የመጀመሪያ ርምጃ ሆኖኗል ብለዋል።

በቅርቡ ወደኢትዮጵያ የተጓዙ ከፍተኛ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር በርካታ ገንቢ ንግግሮችን አካሂደዋል ብለዋል፤ የድርጅቱ የደኅንነት እና ጸጥታ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸኃፊ ጊልስ ሚሾድ፥ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ፊሊፖ ግራንዲ እና ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ ዴቪድ ቢዝሊን ጨምሮ የድርጅቶ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማደረጋቸውን ዘርዝረዋል።

የዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጁ ዴቪድ ቢዝሊ ባወጡት መግለጫ ድርጅታቸው በትግራይ ክልል አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች አጣዳፊ ርዳታ ለማቅረብ መስማማቱን እና በክልሉ ለረድዔት ማጓጓዣ የሚሆን ርዳታ እንዲያደርግ ከኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን ጥያቄ ተቀብለናል ማለታቸውን ዱጃሪክ አስታውሰዋል።

ወደትግራይ ለመግባት አዲስ አበባ ሆነው ፈቃድ እየተጠባበቁ ላሉት ለተቀሩት ስድሳ የረዳኤት ሰራተኞችም ፈቃዱ እንደሚሰጣቸው ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ መንግሥት የርዳታ ሰራተኞች ወደክልሉ እንዲገቡ መፍቀዱ የሚያስደስት ርምጃ ነው ካሉ በኋላ እየተባባሰ ያለው ሰብዓዊ ችግር እና በሲቪሎች ላይ ስለሚደርሱ አስከፊ ጥቃቶች አሁንም የሚደርሱን ሪፖርቶች በጥልቅ ያሳስቡናል ነው ያሉት።

XS
SM
MD
LG