በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፍሪካ ቀንድ ድርቅ ሚሊዮኖች ለቸነፈር መጋለጣቻው ተዘገበ


በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ቆራሄ ዞን፤ ሳጋሎ መንደር አቅራቢያ፣ እኤአ ጃንዋሪ 21/2021
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ቆራሄ ዞን፤ ሳጋሎ መንደር አቅራቢያ፣ እኤአ ጃንዋሪ 21/2021

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዳመለከተው በአፍሪካ ቀንድ የሚታየው ድርቅ ቁጥሩ 13 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ለከባድ ረሃብ ያጋለጣል።

ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያን ጨምሮ “ክልሉ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1981 ወዲህ አይቶት የማያውቅ እጅግ ከፍተኛ ድርቅ እየተጋፈጠ ነው” ሲል ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። ሊከተል የሚችለውን እጅግ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስን ለመመከትም አፋጣኝ እርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አሰምቷል።

ድርቁ በደቡብ እና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምስራቅ እና ሰሜናዊ ኬንያ እንዲሁም በደቡብ-መካከለኛ ሶማሊያ አርብቶ አደር እና አርሶ አደር ማኅበረሰቦችን እየጎዳ ነው።

በክልሉ ያለው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጠን ከፍተኛ መሆኑን ያመለከተው ያለሙ የምግብ ፕሮግራም ቁጥራቸው 4.5 ሚሊዮን ለሚደርስ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለማድረስ እና የከፋ የአየር ንብረት የሚያስከትላቸውን አደጋዎች የበለጠ መቋቋም እንዲችሉ ለመርዳት የ327 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል።

"ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት የበልግ ዝናም ባለመዝነቡ የሰብል ምርት መውደሙን እና ባልተለመደ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው የእንስሳት ሞት አስከትሏል" ሲል ድብሊውኤፍፒ/WFP/ በመግለጫው አመልክቷል።

"የውሃ እና የግጦሽ እጥረት ቤተሰቦችን ቀያቸውን ለቀው እንዲሄዱ እያስገደደ እና በማህበረሰቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነ ነው"

በሚቀጥሉት ወራቶች የሚጠበቀው ከአማካኝ በታች የሆነ የዝናብ መጠን ሁኔታው ከዚህም የከፋ እንዲሆን ያደርገዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል።

ሌሎችም አልፎ አልፎ የኃይል ግጭቶች በሚታዩበት ክልል ተባብሶ ሊቀጥል የሚችለው አደጋ ያሳደረባቸውን ስጋት አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት ድርጅት ባለፈው ወር መገባደጂያ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ብቻ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመጭው የመጋቢት ወር አጋማሽ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በጎረቤት ሶማሊያ ደግሞ ቁጥሩ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚሻ የሶማሊያው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሕብረት አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG