በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን አጋሮቿ ታንክ እንዲልኩላት ጠየቀች


ፎቶ ፋይል፦ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ
ፎቶ ፋይል፦ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ
  • ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ ዕርዳታ ልትልክ ነው

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ምዕራባውያኑን የሀገራቸው አጋሮች “የጦር መሳሪያ ዕርዳታውን በፍጥነት ላኩልን” ሲሉ ተማጸኑ፡፡

ዜሌንስኪ ጥሪውን ያሰሙት ጀርመን በሚገኘው ራምሽታይን የዩናይትድ ስቴትስ የአየር ኃይል ሰፈር ለተሰበሰቡት የሀገራቸው ለጋሾች በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ ጉባዔተኞቹ ሩሲያ ከአንድ ዓመት በፊት የከፈተችባትን ወረራ በመመከት እየተዋጋች ያለችውን ዩክሬንን ለመርዳት ተመራጩ መንገድ የትኛው እንደሆን በመመካከር ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ለጋሾች “ምን ያህል ታንክ እንስጥ በማለት ድርድር ውስጥ ሳይገቡ መላክ ይጀምሩ”ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን ለለጋሾቹ ሀገሮች ባደረጉት ንግግር፣ “ይህ ለዩክሬን ወሳኝ ወቅት ስለሆነ ጠቀም አድርገን እጃችንን መዘርጋት አለብን” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ “የዩክሬን ህዝብ የክሬምሊን የታሪክ ዐይን እኛ ላይ ነው” ብለዋል የመከላከያ ሚንስትር ኦስተን፡፡

በጉባዔው ላይ መላውን የኔቶ አባላት ሀገሮች ጨምሮ የ50 ሀገሮች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ከጉባዔው በፊት ጀርመን እና ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬን የጠየቀቻቸውን ታንኮች መላክ ላይ ቁርጡን ሳይናገሩ ቀርተዋል፡፡ ዜሌንስኪ ሀገራቸው የሚያስፈልጋት ዘመናዊ ታንክ መሆኑን በግልጽ አስታውቀዋል፡፡

ትናንት ማታ ለጉባዔተኞቹ በስልክ ባደረጉት ንግግር ቁርጥ ያለ ውሳኔያችሁን እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጠንካራ ወታደራዊ ድጋፍ እጠብቃለሁ ሲሉ አሳውቀዋቸዋል፡፡

ሩሲያ በበኩሏ ትናንት ባወጣችው መግለጫ “ለዩክሬን ተጨማሪ ታንክ ቢላክ በጦርነቱ ይዞታ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም” ብላለች፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለዩክሬን እንደምትልክ አስታውቃለች፡፡ ይህ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ታንክ አይጨምርም፡፡

XS
SM
MD
LG