የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ዛሬ ረቡዕ የሥራ መልቀቂያ አቀረቡ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩክሬንን በመወከል ታዋቂ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት የ43 ዓመቱ ኩሌባ ከሥልጣን ለመልቀቅ የፈለጉበትን ምክንያት አላቀረቡም፡፡
የመልቀቂያው ጥያቄቸውን ምክር ቤቱ በሚቀጥለው ስብሰባ እንደሚነጋገርበት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ሩስላን ስቴፋንቸክ በፌስ ቡክ ገጻቸው ተናግረዋል፡፡
ኩሌባ መልቀቂያውን ያቀረቡት ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ለጦርነቱ ቀጣይ ወሳኝ ምዕራፍ እየተዘጋጁ ባሉበትና ትልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለውጥ ይኖራል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው፡፡
ዜሌንስኪ ባለፈው ሳምንት ንግግራቸው፣ በመጭው ህዳር ወር 1,000 ቀናት የሚያስቆጥረው ጦርነት ወሳኝ ደረጃ በሚይዝበት ወቅት የካቢኔ አባላት ሹም ሽር አይቀሬ መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ሌሎች አራት የካቢኔ ሚኒስትሮችም ትላንት ማክሰኞ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ሲገለጽ፣ ይህ እኤአ ከ2022 የሩሲያ ወረራ ወዲህ ትልቁ የካቢኔ ለውጥ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በምዕራብ ዩክሬን በምትገኘው ልቪቭ ከተማ በፈጸመችው የሚሳይል ጥቃት ሰባት ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከደረሱት አስከፊ ጥቃቶች አንዱ ነው ተብሏል፡፡
የሚሳይል ጥቃቱን ተከትሎ ኩሌባን ጨምሮ የዩክሬን ባለሥልጣናት ተጨማሪ የምዕራባውያን ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
መድረክ / ፎረም