በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን እና ሩሲያ የሰላም ንግግሮች


የእሳት አደጋ ሠራተኞች በኪየቭ፣ ኦቦሎን አውራጃ በአንድ ህንፃ ላይ በተተኮሰ ጥይት የተነሳውን እሳት ለማጥፋት እየሰሩ እአአ መጋቢት 14/2022
የእሳት አደጋ ሠራተኞች በኪየቭ፣ ኦቦሎን አውራጃ በአንድ ህንፃ ላይ በተተኮሰ ጥይት የተነሳውን እሳት ለማጥፋት እየሰሩ እአአ መጋቢት 14/2022

ዩክሬን እና ሩሲያ ዛሬ የሰላም ንግግራቸውን ቀጥለዋል። በሌላ በኩል ትናንት ሩሲያ የኔቶ አባል ከሆነቸው ከፖላንድ ሃያ ኪሎ ሜትር ብቻ ርቀት ላይ የሚገኝ የምዕራብ ዩክሬን የጦር ሰፈር በተምዘግዛጊ ሚሳይል አጥቅታለች። በዓለም አቀፍ የሰላም ጥበቃ እና ጸጥታ ማዕከሉ ላይ በደረሰው ጥቃት ቢያንስ ሰላሳ አምስት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች አንድ መቶ ሰላሳ አራት ሰዎች እንደቆሰሉ ተዘግቧል።

የዩክሬይን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ትናንት በዕለታዊ ንግግራቸው ያ ጥቃት በሀገራችን "ጨለማ ቀን " ሆኖ አልፏል ብለዋል። የኔቶ ምድቦች የዩክሬንን ወታደሮች በሚያሰለጥኑበት በዚያ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ምዕራባውያን መሪዎች በግልጽ አስጠንቅቄያቸዋለሁ" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሰለቫን ትናንት በሲኤኤን ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ "ይህ አድራጎት የአሜሪካን የሥለላ እና የብሄራዊ ጸጥታ ማኅበረሰብ አላስገረመም" ብለዋል።

አያያዘውም ይህ የሚያሳየው ቭላዲሚር ፑቲን ኃይሎቻቸው እሳቸው ያሰቡትን ዓይነት እርምጃ ስላላስመዘገቡላቸው መበሳጨታቸውን ነው ብለዋል።

ሰለቫን በሲኤስ ቴሌቭዥኝ በሰጡት ቃለ መጠይቅም "ሩሲያ በኔቶ ግዛት ላይ የተኮሰች እንደሆነ የቃል ኪዳን ድርጅቱ አጸፋውን ይመልሳል” ብለው አስጠንቅቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን እና የሩሲያ ልዑካን ሰብዓዊ የሲቪሎች መተላለፊያ ኮሪዶሮችን እና ተኩስ አቁም ሥምምነቶችን በተመለከተ በየቀኑ የሚነጋገሩ ቢሆንም ትናንት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ በሰጡት ቃል ከፑቲን ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካላቸው አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የዩናይድት ስቴትሱ የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪ ሰለቫን እና የመሥሪያ ቢታቸው እና የውጽ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ዛሬ ሮም ላይ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ፖሊት ቢሮ አባል እና የውጭ ጉዳይ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ያንግ ጄይቺ ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ ተዘግቧል።

ውይይቱ በሁለቱ ሀገሮች ፉክክር አያያዝ እና ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት በአካባቢው እና በዓለም ላይ የሚያከትለውን አንድምታ የሚመለከት እንደሚሆን የብሄራዊ ጸጥታ ምክር ቢቱ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

ትናንት የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ለምታካሂደው ጦርነት ቻይናን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያው እርዳታ ጠይቃለች። ቀደም ሲልም ዋይት ሀውስ ቻይናን በሩስያ የተጣለውን ማዕቀብ እንድትተላለፍ ትረጂ እና ብርቱ መዘዝ ይከተልሻል ሲል አስጠንቅቋል።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ኬሚካል የጦር መሳሪያ በሚል እየጨመረ የመጣውን ሥጋት አስመልክተው የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪው ሲናገሩ መቼ እና የት እንደምትፈጽመው ለመተንበይ ያስቸግራል ካሉ በኋላ ሩሲያ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩክሬን በወታደሮቼ ላይ ለመጠቀም ኬሜካል እና ባዮሎጂካዊ መሳሪያ እየሰሩ ነው ማለቷን አንስተዋል።

ይህ የሚያሳየው ሩሲያ ልታደርገው እና በሌሎች ላይ ልታሳብብ መዘጋጀቷን ነው ብለዋል። ሩሲያ መስሪያዎቹን ብትተኩስ ከባድ አጸፋ እንደሚከተላት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ጄክ ሰለቨና ደግመዋል።

የዩክሬይን ፕሬዚዳንት ኔቶ ከበረራ የተከለከለ ቀጣና እንዲያውጅ በድጋሚ ጥሪ አቅርበው ያ ካልሆነ የሩሲያ ሮኬት ኔቶ ግዛት ላይ መውደቁ የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ እንጂ የማይቀር ነው ሲሉ አሳስበዋል።

XS
SM
MD
LG