በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባልነት ጥያቄዋ በአስቸኳይ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጠየቀች


የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎድሜር ዘለንስኪ
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎድሜር ዘለንስኪ

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎድሜር ዘለንስኪ፣ ከሩሲያ ጋር እየተፋለመች የምትገኘው ሀገራቸውን የአውሮፓ ህብረት በአባልነት በአስቸኳይ እንዲቀበል ጥሪ አቀረቡ።

ዘለንስኪ 27 አባል ሀገራት የሉትን ቡድን ለመቀላቀል ያስገቡትን ማመልከቻ ሲፈርሙ የሚያሳይ ፎቶግራፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለቀዋል።

“አብሮነታቸውን ያሳዩንን አጋሮቻችንን በእጅጉ እናመሰግናለን” ፣ ያሉት ዘለንስኪ “ግባችን ግን ከሁሉም አውሮፓዊያን ጋር መሆን ነው። በተለይ ደግሞ እኩል ዕድል ማግኘት። ይህ ፍትሃዊ፣ የሚገባን እና እርግጠኛ ነኝ የሚቻልም ነው” ብለዋል።

በተለመደው ሂደት መሰረት አንድ ሀገር የአውሮፓ ህብረትን ለመቀላቀል ዓመታትን ይፈጅበታል። ሀገራት የአሮፓን መስፍርት እስኪያሟሉ መተግበር ያለባቸው ማሻሻያዎችም አሉ። ዩክሬን ያስገባችው ማመልከቻ ብራሰልስ ለሚገኘው የአውሮፓ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት መድረሱን የዘለንስኪ ቢሮ ኃላፊ አንድሬ ሲባ ተናግረዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን መውሯን ያወገዘው የአውሮፓ ህብረት፣ ለኪቭ የጦር ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፣ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ጥሏል፣ የሩሲያን አውሮፕላኖች ከአውሮፓ ሰማይ ላይም አቅቧል።

የዩክሬን ጥያቄ የተሰማው የአውሮፓ ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሴላ ቮን ደር ሌን ዩክሬናዊያን “እንደ እኛ ናቸው፣ እንዲቀላቀሉን እንፈልጋለን” ማለታቸውን ተከትሎ ነው። ይሁንና የእሳቸው ቃል አቀባይ ኤሪክ ማሜር፣ ይሄን ማለታቸው ዩክሬን በፍጥነት ህብረቱን ትቀላቀል ማለታቸው እንዳልሆነ በትናንትናው ላይ አብራርተዋል። ዘገባው የኤፍፒን ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት፣ ሩሲያ በዩክሬን ሁለተኛ ከተማ ኪርኪያቭ ላይ የሚገኙ ኢላማዎችን መደብደቧ ታውቋል። የሩሲያ ጦር ከዋና ከተማው ኪቭ በስተሰሜን ረጅም ሰልፍ ይዞ እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ተሰምቷል። የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳት የደረሰበትን የካርኪቭ ክልላዊ መንግሥት መስሪያ ቤት የሚያሳይ ቪዲዮ ባጋራበት የቲዊተር መልዕክት ላይ “ዓለም አቀፉን የጦርነት ህግ በመጣስ ሩሲያ ጦርነት አውጃለች” ብሏል።

XS
SM
MD
LG