ብሪታኒያ ውስጥ የተሰበሰቡት የአውሮፓ መሪዎች ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ለዩክሬይን በሚሰጡት ድጋፍ አንድነት እንዲኖራቸው ጥሪ በማቅረብ ጉባኤያቸውን ጀምረዋል፡፡ የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው በቅርቡ ሞስኮ ውስጥ ከሩስያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር የተገናኙትን የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባንን ስማቸውን ሳይጠሩ ነቀፋ ሰንዝረዋል፡፡
ዛሬ ኦክስፈርድ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ብሌንሃይም ቤተ መንግሥት የተጀመረውን የአውሮፓ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ጉባኤ የከፈቱት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር የአውሮፓ ሀገሮች ዩክሬይንን እንደሚደግፉ እንዲያረጋግጡ እና የሩስያን ወረራ በአንድነት እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጉባኤው ላይ በከፍተኛ እንግድነት የተገኙት የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎዶድሚር ዜሌንስኪ የአውሮፓ ሀገሮች ስለሚሰጡት ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸው “ፑቲን በእውነት ጠንካራ ከሆኑ መሪዎች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም” ብለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም