በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ ኃይሎች ከባድ ጥቃቶች እንደፈጸሙ ዩክሬን አስታወቀች


የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪ
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪ

የሩሲያ ኃይሎች የምስራቅ ዩክሬን ከተማ ሲቪዬሮዶኔትስክን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ግፊት በሚያደርጉበት ወቅት ከባድ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ዩክሬን አስታወቀች፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪ ትናንት ማክሰኞ ባስተላለፉት የምሽቱ የቪድዮ መልዕክታቸው፣ በምስራቅ የሉሃንክስ ግዛት ያለውን ወታደራዊ ሁኔታ ሲገልጹ “እርግጥ በአሁኑ ጊዜ እጅግ አስቸጋሪው አካባቢ ነው፡፡ ወራሪዎቹም በዶነቴስክ አቅጣጫ ከፍተኛጫና እየፈጠሩ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ዜለንስኪ አያይዘውም “ሩሲያ የዩክሬን ወታደሮችን ቁልፍ ከሆኑ አካባቢዎች ጠራርጋ ለማስወጣት ጥረት የምታደርገውን ጥረትም አጠናክራለችም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዩክሬን ጦር ኤታማዦር ሹም ቃል አቀባይ በየእለቱ በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሲቪዬሮዶኔትስክ የነበረው ውጊያ ከባድ እንደነበርና ሩሲያ በዩክሬን ጦር ይዞታዎች ላይ የአየርና የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች ማድረጓን ገልጸዋል፡፡

የምስራቅ ዩክሬን ሉሃንስክ አገረ ገዥ ሰሪኺ ሃይዳይ ለአሶሼይትድ ፕሬስ በሰጡት የጽሁፍ አስተያየት “እዚያ ያለው ሁኔታ፣ በቃ ገሃነም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም ነገር በእሳት ጋይቷል፡፡ የከባድ መሳሪያ ድብደባው ለአንዲት ሰዓት እንኳ አይቋረጥም” ብለዋል፡፡

“ዛሬ መቃጠል የሚችለው ነገር ሁሉ እየተቃጠለ ነው” ያሉት ሃይዳይ፣ 500 የሚሆኑ ሲቪሎች በተጠለሉበትና ሲቪዬሮዶኔትስክ ውስጥ በሚገኘው የአዞት የኬሚካል ፋብሪካ ከባድ ውጊያ መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

የሩሲያ ኃይሎች 95 ከመቶ የሚሆነውን የሉሃንስክ ግዛት የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ የዩክሬን ኃይሎች በሲቪዬሮዶኔትስክ የሚገኘውን የአዞት የኬሚካል ፋብሪካ ብቻ ይዘው የሚገኙ መሆናቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ዜለንስኪ የአገሪቱን ምስራቃዊ ግዛት የመከላከሉን አስቸጋሪነት የተገነዘቡ ሲሆን፣ የሩሲያ ኃይሎች በየቦታው ከሚቋቋሟቸው የዩክሬናውያንን ጋር የሚገጥማቸው ፍልሚያ ግን የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል፣ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂነት ላይ የሚያተኩር ቡድን መቋቋሙን ለማብሰር፣ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ፣ ከዩክሬን አቃቢ ህግ ጀኔራል አርያና ቬኔዲክቶቫ ጋር፣ ዩክሬን ለቪቭ ውስጥ ትናንት ማክሰኞ መገናኘታቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ጋርላንድ ለሪፖርተሮች በሰጡት መግለጫ “ዩናይትድ ስቴትስ የማያወላዳ መልዕክት እያስተላለፈች ነው፡፡ ምንም መደበቂያ ስፍራ አይኖርም፡፡ እኛ፣ እኛና አጋሮቻችን፣ ለእነዚህ ግፎች ኃላፊነት ያለባቸው ሁሉ ተጠያቂ መሆናቸውን ለማረጋገጥ፣ የተገኘውን ማናቸውንም መንገድ ሁሉ እንጠቀማለን” ብለዋል፡፡

“የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነት” ቡድኑ ዩክሬንን በወንጀል ክስ፣ በሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ በጦር ወንጀሎችና በሌሎች ጭካኔዎች፣ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማጣራቱ ሂደት እንደሚረዳ የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ቡድኑን በአማካሪነት የሚመሩትም የቀድሞ የናዚ ጦር ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ የተደረገውን ጥረት የመሩት ኤሊ ራዝንባም መሆናቸውን ፍትህ ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG