የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ውጊያው አቁመው የርዳታ አቅርቦት እንዲገባ እንዲፈቅዱ የጠየቀችው ብሪታኒያ የተቀሩት የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት አባላትን ድጋፍ እንደምትጠይቅ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሯ አስታውቋል፡፡
ብሪታኒያ የወቅቱ የምክር ቤቱ ተረኛ ፕሬዝደንት ናት። ዛሬ ሰኞ የምክር ቤቱን ስብሰባ በሊቀመንበርነት የሚመሩት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ዴቪድ ላሚ ሀገራቸው ና ሲየራሊዮን በጋራ ያቀረቡት ረቂቅ ውሳኔ ላይ ድምጽ ያሰጣሉ፡፡
ውሳኔው ከርዳታ አቅርቦት መግባት ሌላ ለሲቪሎች ደህንነት ጥበቃ እንዲሰጥም ይጠይቃል፡፡
ሚንስትሩ ብሪታኒያ ሱዳን እንድትረሳ እንደማትፈቅድ እና ርዳታዋንም በእጥፍ በማሳደግ ወደ285 ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንድምታደርግ እንደሚያስታውቁ መግለጫው አመልክቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዴቪድ ላሚ ከዚህ በተጨማሪ እስራኤል ወደጋዛ የሚላከውን የሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት መገደቧን እንደሚነቅፉ መግለጫው አውስቶ በአስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ታጋቾቹ በሙሉ እንዲለቀቁ ይጠይቃሉ ብሏል፡፡
ዩክሬይንን በተመለከተም ሩስያ ያለው ዕውነታ እስከሚገባት ብሪታኒያ ከዩክሬን ጋር መቆሟን እንደምትቀጥል እንደሚናገሩ መግለጫው አመልክቷል፡፡
መድረክ / ፎረም