አጨቃጫቂ የሆነውንና እንግሊዝ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያላትን ዕቅድ በተመለከተ ለመነጋገር የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ቅዳሜ ሩዋንዳን ጎብኝተዋል።
የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሱኤላ ብሬቨርማን ከሩዋንዳው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሰንት ቢሩታ ጋር ከተገናኙ በኋላ በዕቅዱ አስፈላጊነት ላይ ተነጋግረዋል። ስደተኞቹ ለብዝበዛ የሚጋለጡበትን መንገድ ይቀንሳል ሲሉ ተደምጠዋል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሯ።
የእንግሊዝ ወግ አጥባቂ መንግሥት ወደ አገሪቱ የሚደረገውን ፍልሰት ማቆም ይሻል፡፡ አዲስ ፍልሰትኞች ወደ አገሪቱ ለመግባት እንዳይሞክሩ በሚል ወደ ሩዋንዳ ተላልፈው የሚሰጡበት ስምምነትን ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ዓመት ተፈራርመዋል።
ባለፈው የፈረጆች ዓመት ከ45 ሺህ በላይ ፍልሰተኞች በጀልባ እንግሊዝ ገብተዋል። ከሁለት ዓመት በፊት እንግሊዝ የገቡት ፍልሰተኞች ቁጥር 8 ሺህ 500 ነበር።
በአዲሱ ዕቅድ መሠረት በጀልባ ወደ እንግሊዝ የሚገቡ ፍልሰተኞች ተይዘው ወደ ሩዋንዳ ይወሰዳሉ። የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካገኘ ሩዋንዳ እንዲቆዩ ይፈቀድላቸዋል።
170 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለው ዕቅድ ሕጋዊ ሙግት የገጠመው ሲሆን፣ እስከአሁን በዕቅዱ መሠረት ወደ ሩዋንዳ የተላከ ፍልሰተኛ የለም።