በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሪታንያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለማጓጓዝ በሰው 215ሺሕ ዶላር እንደሚያስከፍል አስታወቀች


ፎቶ ፋይል፦ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱና ለንደን፣ ብሪታንያ እአአ ግንቦት 4/2023.
ፎቶ ፋይል፦ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱና ለንደን፣ ብሪታንያ እአአ ግንቦት 4/2023.

ብሪታንያ፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለማጓጓዝ ያወጣችው ዕቅድ፣ በነፍስ ወከፍ ከ215ሺሕ የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚያስወጣት አስታወቀች፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ወግ አጥባቂ መንግሥት፣ ባለፈው ዓመት፣ ከመካከለኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ጋራ ባደረገው ስምምነት፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ ይፈልጋል።

ለዚኸም የመጀመሪያ ዝርዝር ጥናት ያካሔደ ሲኾን፣ በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ አውሮፓ የሚጎርፉትን ስደተኞች ቁጥር ለመቀነስ እና በተመሳሳይ አኳኋን ከፈረንሳይ የሚመጡትን ጥገኝነት ጠያቂዎች ለመከላከል እንደሚያስችል አምኖበታል፡፡

ለጥገኝነት ጠያቂዎች ችግር መፍትሔ እንዲያመጡ፣ ከራሳቸው ፓርቲ ወግ አጥባቂ ሕግ አውጪዎች እና ከሕዝብ ግፊት እየተደረገባቸው ያሉት ሱናክም፣ ቅድሚያ ከሚሰጧቸው አምስት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እንዲኾን አድርገዋል።

ትላንት ሰኞ ታትሞ በወጣው፣ የኢኮኖሚ ተጽእኖ ግምገማ ግን፣ እያንዳንዱን ግለሰብ ወደ ሩዋንዳ ለመላክ፡- በአማካይ ለሩዋንዳ መንግሥት የሚከፈል 133ሺሕ485 ዶላር፣ ለበረራ እና ለአጃቢ 28ሺሕ ዶላር እና ለሥራ ማስኬጃ እና ሕጋዊ ወጪዎች 22ሺሕ882 ዶላር እንዲሚያስወጣ መንግሥት አስታውቋል።

የብሪታንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱዌላ ብሬቨርማን፣ እነዚኽ ወጪዎች፥ ወደ ብሪታንያ ለመድረስ የሚሞክሩ ሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመከላከል ካለው ጠቀሜታ እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማኖር ከሚወጣው እየጨምረ ያለ የቤት ዋጋ አንጻር መታየት አለባቸው፤ ብለዋል።

እንደ ብሬቨርማን ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት፣ ለጥገኝነት ጠያቂዎች መኖሪያ ቤት፣ በዓመት የሚወጣው 4ነጥብ5 ቢሊየን ዶላር፣ በመጪው ዓመት፣ ወደ 13ነጥብ6 ቢሊየን ዶላር ከፍ ይላል።

የስኮትላንድ ብሔራዊ ፓርቲ በበኩሉ፣ የብሪታንያ መንግሥት፣ በሀገር ውስጥ እየጨመረ በመጣው የቤት እና የምግብ ዋጋ የተቸገሩ ሰዎችን በበቂ ሳይረዳ፣ ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን ከሀገር ለማስወጣት፣ “እጅግ በጣም ግዙፍ” ገንዘብ ማውጣቱን ተችቷል።

ባለፈው ዓመት፣ ከፈረንሳይ የተነሡ 45ሺሕ ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ በአነስተኛ ጀልባዎች ተጭነው ወደ ብሪታንያ ሲገቡ፣ በዚኽ ዓመት ደግሞ፣ እስከ አሁን ከ11ሺሕ በላይ ሰዎች እንደገቡ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG