በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ የብሪታንኒያ ዕቅድ ሕገ ወጥ እንደሆነ ፍርድ ቤት ወሰነ


የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ

የብሪታኒያ መንግሥት፣ አደገኛ ጉዞ አድርገው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፤ ያላቸውን ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያወጣው ዕቅድ፣ በአገሪቱ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፥ ሕገ ወጥ ነው፤ ተባለ።

በሦስት ዳኞች የተሠየመው የአገሪቱ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ “ሩዋንዳ፥ የፍልሰተኞቹ ደኅንነት የሚጠበቅባት ሦስተኛ አገር አይደለችም፤” ሲል፣ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል። ውሳኔውን ያልተቀበለው መንግሥት፣ የይግባኝ አቤቱታ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የሚመራው ወግ አጥባቂ መንግሥት፣ በአነስተኛ ጀልባዎች ላይ በመሆን፣ ከሰሜን ፈረንሳይ እየተነሡ ወደ እንግሊዝ ገብተው ለመኖር የሚፈልጉትን ፍልሰተኞች እንደሚያስቆም በተደጋጋሚ ዝቷል።

ባለፈው ዓመት፣ 45ሺሕ ሰዎች የእንግሊዝን መተላለፊያ ቻነል አቋርጠው ሲገቡ፣ በርካቶች ለማቋረጥ ባደረጉት ሙከራ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ከፈረንሳይ ተነሥተው ባሕሩን አቋርጠው፣ በእንግሊዝ መተላለፊያ ቻነል በኩል ወደ አገሪቱ የገቡትን ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ለመላክ፣ መንግሥት ከስምምነት ላይ ቢደርስም፣ ሰዎችን መኖር ወደማይፈልጉበት አገር የመላኩ ውጥን፣ ኢሞራላዊ እና ኢሰብአዊ ተግባር ነው፤ በማለት የመብት ተሟጋቾች ተቃውሞ አሰምተዋል።

XS
SM
MD
LG