ዋሽንግተን ዲሲ —
ዩጋንዳ ውስጥ 48 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ፣ በአንድ አውቶብስ ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ አንድ ሰው መሞቱን የሃገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ፍንዳታው የደረሰው ትናንትና ሰኞ ከካምፓላ ወደ ምዕራባዊ ዩጋንዳ ግዛት ሲጓዝ በነበረው አንድ አውቶብስ ውስጥ ነው፡፡
ፖሊስ የአደጋውን መንስኤ እየመረመረ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜም ከካምፓላ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ አንድ ሰው ተገድሏል፡፡
ለቅዳሜው ጥቃት የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን፣ ቦምቡን ያፈነዳው ቦታው “በዩጋንዳ መንግሥት ሰዎችና ሰላዮች የሚዘወተር በመሆኑ ነው” ብሏል፡፡
የዩጋንዳው መሪ ፕሬዚዳንት ሙሲቬኒ በሰጡት መግለጫ፣ የቅዳሜው ጥቃት የሽብርተኞች ድርጊት እንደሚመስል ገልጸው፣ “የአሳማ ሥጋ ወደ ሚሸጥበት መመገቢያ ስፍራ የገቡ ሶስት ሰዎች በላስቲክ የተጠቀለለ ነገር አስቀምጠው እንደወጡ ፍንዳታው መድረሱን” ተናግረዋል፡፡