የዩናይትድ ስቴትስ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለኡጋንዳ መስጠቷን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሬ አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ በሚኒስቴሩ ድረ ገጽ ላይ ባወጣው መግለጫ ርዳታው የሚሰጠው “በዩናይትድ ስቴትስ የስነ ሕዝብ፣ የስደተኞች እና የፍልሰት ቢሮ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማትና ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤድ) በኩል መሆኑን አስታውቋል፡፡
ተጨማሪው ሰብአዊ ርዳታ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዩጋንዳ ላሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መርጃ እንደሚውል መግለጫው አመልክቷል፡፡
ይህ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እ አ አ ባለፈው 2023 የበጀት ዓመት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለዩጋንዳ የሚሰጠውን የአሜሪካን ሰብዓዊ እርዳታ ከ178 ሚሊዮን ዶላር በላይ አድርሶታል፡፡
እርዳታው በዩጋንዳ ውስጥ ለሚገኙ ከ1ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እና የአካባቢ አስተናጋጅ ማህበረሰቦችን ጤና፣ ትምህርት፣ ጥበቃን፣ የምግብ እርዳታ እና የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለማቅረብ እንደሚረዳም ተመልክቷል፡፡
ዩጋንዳ ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ስደተኞችን የምታስተናግድ ሀገር ናት፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ በዋናነት ከደቡብ ሱዳን፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከሶማሊያ እና ከሱዳን የመጡ ከ130፣000 በላይ አዲስ ስደተኞችን ተቀብላለች።
“ዩናይትድ ስቴትስ በዩጋንዳ ትልቁ የሰብአዊ ርዳታ ለጋሽ እንደሆነች ትቀጥላለች” ያለው መግለጫው “በሀገሪቱ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙትን ስደተኞች መደገፏን ትቀጥልበታለች” ብሏል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ መግለጫ “ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች ለጋሾችም በመላው ቀጠና በግጭትና በሌሎች ቀውስ እየተጎዱ ያሉትን ሁሉ የሚረዱትን እንደ ዓለም ምግብ ድርጅት፣ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነርና አጋር ሰብዓዊ ድርጅቶች እንዲደግፉ ታሳስባለች” ብሏል፡፡
መድረክ / ፎረም