በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩጋንዳ መዲና የደረሱ ተከታታይ ጥቃቶች የተነሳ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ጨመረ


የዩጋንዳ ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት ላይ የደረሰውን ጥቃት ሲመረምሩ
የዩጋንዳ ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት ላይ የደረሰውን ጥቃት ሲመረምሩ

የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃል ገብተዋል

እሁድለት በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ የአለም ዋንጫ ፍጻሜን በመከታተል ላይ በነበሩ የኳስ አፍቃሪያን ላይ የደረሱ ተከታታይ ጥቃቶች 76 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ ያደረገው የዩጋንዳ ፖሊስ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ኒው ቪዥን የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ዛሬ አስነብቧል።

በአለም ዙሪያ ከሀገር መሪዎች እስከ ፊፋ ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ የተጎጅ ቤተሰቦችና ሰላም ወዳድ ሰዎችን ያስቆጣው የሽብር ተግባርን የሶማሊያው አል-ሸባብ ሀላፊነት ወስዶበታል።

በሞቃዲሾ ለጋዜጠኞች ቃሉን የሰጠው በቅጽል ስሙ አሊ ዲሬ በመባል የሚታወቀው የአል-ሸባብ ቃል አቀባይ አሊ ሞሀመድ ሬጌ “ዩጋንዳና ሌሎች ለአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ወታደር ያዋጡ አገሮች ቡሩንዲን ጨምሮ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ የተላለፈውን ጥሪ ሳይቀበሉ ቆይተዋል። የእሁዱ ጥቃት የታለመው አል-ሸባብ በካምፓላና ቡጂንቡራ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ ለማሳየት ነው። ወታደሮቹ ከሶማሊያ ካልወጡ ጥቃቱ ይቀጥላል፣” ብሏል።

ዩጋንዳ በሶማሊያ ከሚገኘው የ6,100 የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ መሀል ግማሹን ያዋጣች አገር ናት። ይሄ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅናና ድጋፍ የሚሰጠው የሰላም ጓድ አብዛሀኛውን የአገሪቱን ክፍል በአክራሪ የእስላማዊ አንጃዎች ለተቀማው የሽግግር መንግስት ድጋፍ ይሰጣል።

በጥቃቶቹ ቦታዎች የተገኘ የፈንጂ አካል
በጥቃቶቹ ቦታዎች የተገኘ የፈንጂ አካል

የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጥቃቱ የደረሰባቸውን የካያዶንጎ ራግቢ ክለብና የኢትዮጵያዊያን የገጠር ምግብ ቤት ከጎበኙ በኋላ በሰጡት ቃል ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃል ገብተዋል። አክለውም አገራቸው በሞቃዲሹ ካላት ሀላፊነት አታፈገፍግም፤ እንዲያውም አጠናክራ ትቀጥልበታለች ብለዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት ሁለት የአጥፍቶ ጠፊዎች እንደሆኑ የፖሊስ የቅድመ-ምርመራ ግኝቶች ጠቁመዋል።

በዚህ ጥቃት በአብዛሃኛው የሞቱት ዩጋንዳዊያን ሲሆኑ 14 የውጭ አገር ዜጎች ህይወታቸው አልፏል። ከነዚህም አንድ ኢትዮጵያዊ ከ6-9 የተገመቱ ኤርትራዊያን፣ አንድ አሜሪካዊና ለጊዜው ያልታወቁ የሌላ አገር ዜጎች መኖራቸው ተጠቁሟል። የአገሪቱ ፖሊስ የምርመራ ውጤቱን እስኪያጠናቅቅ ድረስ እነዚህ ቁጥሮች የተረጋገጡ አይደሉም።

XS
SM
MD
LG