የዩጋንዳ መንግሥት በኢቦላ ወረርሽኝ እስካሁን 23 ተማሪዎች መያዛቸውን እና ከመካከላቸው 8ቱ መሞታቸውን ተከትሎ የሀገሪቱን ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ዐመት መጨረሻ ከታቀደው የጊዜ ሰሌዳ አስቀድሞ ለመዝጋት መወሰኑ ተገለጠ።
ትምህርት ቤቶቹን ከጊዜ ሰሌዳው በሁለት ሳምንት ቀደም ብለው እአአ ህዳር 25 ለመዝጋት ስለተደረገው ውሳኔ የትምህርት ሚስትር ደኤታዋ ጆይስ ሞሪኩ ካዱሱ ትናንት አስታውቀዋል።
በትምህርት ሚኒስቴሩ መሠረት ዋና ከተማዋ ካምፓላ እንዲሁም ዋኪሶ እና ሙቤንዴ በተባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ለኢቦላ የተጋለጡ ተማሪዎች ተገኝተዋል።
የፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ካቢኔ በመላ ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ የወሰነው ተማሪዎች በብዛት አብረው የሚውሉበት ሁኔታ ለበሽታው መዛመት አመቺ እንዳይሆን በመስጋት መሆኑን የትምህርት ሚንስትር ደኤታዋ አስረድተዋል።
ለኢቦላ የተጋለጡት ተማሪዎች የተገኙባቸው ትምህርት ቤቶች የታጠሩ ሲሆን ተማሪዎች ከአዲሱ የአውሮፓ ዓመት በኋላ እስኪመለሱ በትምህርት ቤቶች አስፈላጊው የጽዳት ስራ እንዲከናወን መመሪያ ተሰጥቷል።
ብዙዎች ቤተሰቦች ትምህርት ቤቶች ቀደም ብለው የሚዘጉ መሆኑ አሳዝኗቸዋል። በኮቪድ አስራ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች ለሁለት ዐዓመታት ተዘግተው ከርመው እንደነበር ይታወሳል።