በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዑጋንዳ ለኢቦላ የተጋለጡት ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ ደረሰ


አንድ የጤና ሰራተኛ በሙላጎ ሪፈራል ሆስፒታል የኢቦላ ክትባት ጠርሙስ ለመስጠት በዝግጅት ላይ፤ በካምፓላ፣ ዑጋንዳ እአአ 3/2025
አንድ የጤና ሰራተኛ በሙላጎ ሪፈራል ሆስፒታል የኢቦላ ክትባት ጠርሙስ ለመስጠት በዝግጅት ላይ፤ በካምፓላ፣ ዑጋንዳ እአአ 3/2025

በዑጋንዳ በገዳዩ የኢቦላ ወረርሽኝ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ መድረሱን የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ።

የምሥራቅ አፍሪቃዊቱ አገር ‘ኢቦላ ሱዳን’ በተባለው እና እስካሁን የመከላከያ ክትባት ባልተበጀለት የቫይረሱ ዝርያ ስትጠቃ ያሁኑ ስድስተኛዋ ነው።

ባለፈው ጥር ወር መገባደጃ ላይ ነበር ዋና ከተማይቱ ካምፓላ ላይ አንዲት ነርስ በዚሁ ሕመም ሳቢያ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ ወረርሽኝ መቀስቀሱ የተረጋገጠው።

ዲያና አትዊን የተባሉ አንዲት የዑጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሲናገሩት "ከመጀመሪያዎቹ ሶስት ተጋላጮች በኋላ አጠቃላይ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ዘጠኝ መድረሱን አረጋግጠናል" ብለዋል። አያይዘውም “ለወረርሽኙ የተጋለጡት በሙሉም ቀደም ሲል በዚሁ ሳቢያ ለህልፈት ከተዳረገችው ነርስ ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

አትዊን፤ የበሽታው መዛመት "በቁጥጥር ስር ውሏል" ቢሉም ወረርሽኙ የማያሰጋ መሆኑ እስኪገለጥ ድረስ የዑጋንዳ ሕዝብ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።

በካምፓላ እና በምሥራቃዊቱ ምባሌ በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ ጠቅላላ ቁጥራቸው 265 የሚደርሱ ለቫይረሱ ተጋልጠው ሊሆን ይችላል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ከሌሎች ተለይተው እንዲቆዩ ተደርገዋል። በወሩ መጀመሪያ ላይ እዚያው ዑጋንዳ ውስጥ የክትባት ሙከራ ሥራ መጀመሩም ይፋ ተደርጓል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG