ዩጋንዳ በመጪው የካቲት ወር በምታካሂደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ዛሬ ሰኞ በይፋ የምረጡን ዘመቻቸውን ጀምረዋል።
የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች የዩጋንዳ መንግሥት የውድድሩን ሜዳ ለሁሉም እኩል ያደላድል ዘንድ ኣሳስቡዋል።
በፕሬዚደንታዊ ምርጫው እንዲወዳደሩ የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ፈቃድ ከሰጣቸው መካከል ኣንዱ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ሲሆኑ ለአምስተኛ ጊዜ በስልጣን ላይ ለመቆየት ይወዳደራሉ።
ተቃዋሚው መሪ ኪዛ ቢሲጄ በበኩላቸው ፕሬዚደንት ሙሴቬኒን ስልጣን ለማስለቀቅ ሲሞክሩ ኣራተኛ ሙከራቸው ይሆናል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ትናንት ዕሁድ ምሽት ባወጣው መግለጫ ፖሊሶች የሚፈጽሙት ጭካኔ የተመላበት ኣድራጎት፡ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ወከባና እና ካሁን ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች በደርሱ በደሎች ተጠያቂነት ኣለመኖሩ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሂደት ኣውን እንዳይሆን ዕንቅፋት መፍጠሩን ኣመልክቱዋል።
የሂዩማን ራይትስ ዋች ከፍተኛ የኣፍሪካ ተመራማሪ ማሪያ ቤርኔት “ይህ የምርጫ ዘመቻው፡ ወቅት ባለፉት ዘመቻዎች የታየው ኣፈና ፡ ጥቃት ፡ የፖሊስ የጭካኔ ርምጃ እንዳይደገም ለመከላከል ዕድል የሚሰጥ ወሳኝ ወቅት ነው” ብለዋል። “ ዩጋንዳውያን በሙሉ ህዝባዊ ስብሰባዎች መካፈል፡ በኣካል ተገኝተውም ሆነ በሬዲዮ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የሚናገሩትን መስማትና ያለምንም ማመንታትና ፍራቻ ሃሳባቸውን መግለጽ መቻል ይኖርባቸዋል” ብለዋል።
ሙሉውን ዝርዝር ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።