በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ ሦስት የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች ባልደረባቸው ተገደሉ


ፎቶ ፋይል፡ ሞቃዲሾ
ፎቶ ፋይል፡ ሞቃዲሾ

በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ሦስት አባላት በዩጋንዳዊ ባልደረባቸው ተተኩሶባቸው መገደላቸውን የዩጋንዳ የጦር ኃይል አስታወቀ።

የዩጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች ቃል አቀባይ ብሪጋዲየር ጄኔራል ፌሊክስ ኩላዪጊዬ በሰጡት መግለጫ "ወታደሩ ሰኞ ጠዋት ከእንቅልፉ ተነስቶ ባልደረቦቹ ላይ ጥይት አርከፍክፎባቸዋል" ብለዋል።

አራቱም የሞቃዲሾ የአውሮፕላን ጣቢያ ጥበቃ አባላት እንደነበሩም ባለሥልጣኑ ገልጸዋል። አጥቂው በቁጥጥር ስር መዋሉን እና ወደዩጋንዳ ተወስዶ የጦር ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አክለው ገልጸዋል።

"ሰውየው የጭንቀት ወይም ሌላ የአዕምሮ ጤና ችግር ይኖረው እንደሆን አላወቅንም" ያሉት ባለሥልጣኑ ባልደረቦቹ ላይ ተኩስ የከፈተበትን ምክንያት የሚመረምር ቦርድ መቋቋሙን አመልክተዋል።

ዩጋንዳ እአአ ከ2007 ጀምራ የሶማሊያን መንግሥት ለመገልበጥ የተነሱ ታጣቂዎችን የሚዋጉ ወታደሮች አሰማርታለች።

ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲም በአፍሪካ ህብረቱ የሶማሊያ ሽግግር ተልዕኮ ኃይል ውስጥ ወታደሮች አሏቸው።

እአአ በ2019 አንድ ዩጋንዳዊ ሰላም አስከባሪ የበላይ አለቃውን ተኩሶ ከገደለ በኋላ ራሱን መግደሉን ዜናው ጠቅሷል።

ከዚያ ቀደም ብሎ በ2017 ዩጋንዳ ውስጥ በወታደሮች በየመንገዱ የሚገደለው ሰው ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ የሀገሪቱ የአዕምሮ ጤና ሆስፒታል ጭንቀት ያለባቸው ወታደሮች በተለይም ሶማሊያ ውስጥ ላገለገሉ ወታደሮች የህክምና ዕርዳታ የሚሰጥ ክፍል ማቋቋሙን ዜናው ጨመሮ አውስቷል።

XS
SM
MD
LG