የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በካርቱም በሚገኘው የአምባሳደሯ መኖሪያ ቤት ላይ፤ “አስከፊ” ያለችው ጥቃት ተፈጽሟል ማለቷን የሱዳን ሠራዊት ዛሬ ውድቅ አድርጓል። ሠራዊቱ ለጥቃቱ ተቀናቃኙን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ተጠያቂ አድርጓል።
“አሳፋሪና የፈሪ” ያለው ድርጊት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተፈፀመ ነው ሲል የሱዳን ሠራዊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሱዳን ወታደራዊ አውሮፕላን በአምባሳደሩ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ፈጽሟል ስትል ኤምሬትስ ዛሬ ማለዳ አስታውቃ ነበር። የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ እንዳለው፣ በአምባሳደሩ መኖሪያ ቤት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በህንጻው ላይ አስከፊ ጉዳት አስከትሏል፡፡
የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የኤምሬት ስንክስ “የሃሰት ክስ” ሲል ገልፆታል።
ለ17 ወራት በቀጠለው ጦርነት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በመሣሪያና በሌሎች መንገዶች ትደግፋለች ሲል የሱዳን ሠራዊት በተደጋጋሚ ከሷል፡፡ ይሁን እንጂ የገልፏ ሀገር ክሱን አጣጥላለች፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት የማዕቅብ ቁጥጥር፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ትደግፋለች የሚለው ክስ ተአማኒነት እንዳለው አስታውቋል።
ወደ ነጻ ምርጫ የሚደረገውን ሽግግር በተመለከተ በተፈጠረው አለመግባባት በሱዳን ጦር ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ከጎርጎሮሳዊያኑ ሚያዚያ 2023 ጀምሮ ጦርነት በመካሄድ ላይ ነው። የመንግስታቱ ድርጅት ወደ 25 ሚሊየን የሚደርሱ ሱዳናዊያን፣ ማለትም ግማሽ የሚሆነው የሃገሪቱ ሕዝብ በአስከፊ ረሃብ ውስጥ በመሆኑ ድጋፍ ያስፈልገዋል ብሏል፡፡ በተጨማሪም ስምንት ሚሊየን ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም