ዋሺንግተን ዲሲ —
የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት የነበራት ተሳትፎ ማቆሟን ተከትሎ በኤርትራ አሰብ ላይ የነበራትን ወታደራዊ መደብ በከፊል እየነቃቀለች መሆኗን የሳተላይት ምስሎች ማሳየታቸውን አሶሼየትድ ፕሬስ ዘገበ።
ኤሚሬትስ በየመኑ ጦርነት ከሳውዲ መራሹ ጥምረት ጎን ሆና በኢራን ከሚታገዙት ከሁቲዎቹ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ስትዋጋ ቆታለች።
እአአ 2015 መስከረም ወር ላይ አሰብ ላይ በገነባችው ወደብና የአውሮፕላን ማረፊያ እና መንደርደሪያ ከባድ መሳሪያዎችንና የሱዳን ወታደሮችን ወደየመን ለማጓጓዝ ተጠቅማበታለች።
ሃገሪቱ ከየመኑ ጦርነት መውጣቱዋን ተከትሎ አሰብ ላይ ካላት ወታደራዊ ሰፈር መሳሪያዎችን ነቃቅላ ማንሳቷንና አዲስ የተገነቡ ጣቢያዎችን ጭምር ማፈራረሷን የሳተላይት ምስሎቹ እንዳመለከቱ የኤፒ ዘገባ ገልጿል።
አሶሽየትድ ፕሬስ ለኤሚሬትስ ባለሥልጣናት ላቀረበው ጥያቄ መልስ እንዳላገኘ አስታውቋል። በአሰብ ወደብ እንድትጠቀም የሦላሳ ዓመት ኮንትራት ከሰጠቻት ከኤርትራም በኩል ምላሽ ለማግኘት ዋሽንግተን ለሚገኘው ኤምባሲዋ ላቀረብነው ጥያቄ መልስ ለማግኘት አልቻልንም ብሏል።