በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ዩናይትድ ስቴትስ ከታንዛኒያ ጋር የንግድ ግንኙነቷን ታጠናክራለች" - ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ


የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ
የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ሀገራቸው ከታንዛኒያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላት አስታወቁ፡፡

ሃሪስ ትናንት ሀሙስ ጉብኘታቸውን ሲያጠናቅቁ ከታንዛኒያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉ ሀሰን ጋር ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በታንዛኒያ ኢኮኖሚ እና መዋዕለ ነዋይ ለማሳደግና የምጣኔ ሀብት ትስስራችንን ለማጎልበት አብሮ መስራትን የጋራ ግባችን አድርገናል” ብለዋል፡፡

ለዚህም በርካታ ዕቅዶች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፣ የዩናይትድ ስቴትስ አስመጪና ላኪ(EXIM) ባንክ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት መጠን ለማሳደግ እንዲሰራ ከአዲስ የመግባቢያ ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች፣ ወደታንዛኒያ ለመሰረተ ልማት፣ ለትራንስፖርት፣ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ለአየር ንብረት፣ ለኃይል ደህንነትና የኃይል አመንጪነት ዘርፍ የሚውሉ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን እንዲልኩ፣ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ላሉት ለዚህ ባንክ፣ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥም ሃሪስ አስረድተዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ለታንዛኒያ የ560 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ቃል የገባች ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ዘገቧል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቷ የታንዛኒያ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዛምቢያ ያቀኑ ሲሆን የፊታችን እሁድ ወደ ዋሽንግተን እንደሚመለሱ ተዘግቧል፡፡

XS
SM
MD
LG