በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የ18 ወራት ጊዜያዊ ከለላ ተሰጠ


የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዛሬ ዋሽንግተን ዲሲ
የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዛሬ ዋሽንግተን ዲሲ

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከትናንት፣ ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለ18 ወራት ለሚቆይ ጊዜ ጊዜያዊ የከለላ ፍቃድ እንዳላቸው የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የዚህ ለአንድ ዓመት ተኩል የሚቆይ ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል።

“ዩናይትድ ስቴትስ፣ እየተካሄደ ያለው ግጭትና ኢትዮጵያን የተጫናትን ጊዜያዊ ሁኔታዎችን ይገነዘባል። የደኅንነት መሥሪያ ቤቱም ከለላ ለሚያስፈልጋቸውና በአሜሪካ ላሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ግዜያዊ ከለላ ለመስጠት ይፈልጋል” ብሏል መግለጫው።

“በግጭት፣ በሰብዓዊ ቀውስ፣ በምግብ እጥረት፣ በጎርፍ በድርቅ እና በመፈናቀል ምክንያት ወደ ሃገራቸው መመለስ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ያለው ሁኔታ እስከሚሻሻል በአሜሪካ እየሰሩ መቆየትና መሥራት ይችላሉ” ብሏል የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በመግለጫው።

“በመካሄድ ላይ ባለ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም ለየት ያሉ እና ግዜያዊ ችግሮች ከሚባሉት ሦስት ሁኔታዎች በአንዱ ወይም ከአንድ በላይ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ጊዜያዊ የከለላ ፈቃድ ይሰጣል” ብሏል መግለጫው። ኢትዮጵያ “በመካሄድ ላይ ባለ ጦርነትና ለየት ያሉ እና ግዜያዊ ችግሮች” የሚለውን ስለምታሟላ ከለላው መሰጠቱን የደህንነት መ/ቤቱ አስታውቋል።

በትጥቅ ግጭቱ ምክንያት ሲቪሎች ለጥቃት፣ ለሞት፣ አስገድዶ ለመደፈርና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች፣ በጎሳ ላይ ለተመሠረት ጥቃት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጥቃቶች ሊጋለጡ ይችላሉ ብሏል መግለጫው።

ግዚያዊ የከለላ ፈቃድ ለኢትዮጵያውያን ሲሰጥ ለመጀመሪያ ግዜ መሆኑ ታውቋል።

ከትናንት ጥቅምት 10 በፊት አሜሪካ የገቡ ኢትዮጵያውያን የከለላው ተጠቃሚ ናቸው። ከትናንት ወዲህ አሜሪካ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ግን የከለላው ተጠቃሚ እንደማይሆኑ መግለጫው አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG