የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ዛሬ ከናሚቢያ ወደኬንያ አቅንተዋል። በዚያ የሚያደርጉት ጉብኝት በሴቶች ዓቅም ግንባታ እና ህጻናትን በሚመለከቱ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን እንደገና አብዝቶ እያጠቃ ባለው የረሃብ ቀውስ ላይ የዓለምን ትኩረት በመሳብ እንደሚጠቅም ተስፋ አድርገዋል።
ሚሲስ ባይደን ትናንት ሀሙስ በናሚቢያ ጉብኝታቸው ባደረጉት ንግግር በዓለም ዙሪያ ላሉ አጣዳፊ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ የአፍሪካ ድምጽ ወሳኝ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል።
"የአፍሪካውያን ድምጽ እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ቡድን 20 በመሳሰሉ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን በጋራ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ጉዳዮች ሁሉ ከአፍሪካውያን ጋር እኩል በአጋርነት እንደምንሰራ እናረጋግጣለን" ብለዋል።
ሴቶች እና ወጣቶች በማብቃት፣ የዓለም አቀፍ ጤና ጥበቃን በማጠናከር እና በኢኮኖሚ ግንባታ ዘርፎች አብረን እንሰራለን ሲሉ ጂል ባይደን ተናግረዋል።