በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያን የተፈላጊ ሰዎች ጥያቄ “ከሕግ አኳያ እያየሁት ነው” አለች


በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ጋራ
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ጋራ

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ጋራ፣ ባለፈው ሳምንት ተገናኝተው መነጋገራቸውን፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ እና የፌደራል ፖሊስ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ግንቦት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መግለጫ፣ በአሜሪካ የሚኖሩና በኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈለጉ ሰዎች ጉዳይ በኮሚሽነሩ መነሣቱን አመልክቷል።

ኮሚሽነሩ፣ “የአገራችንን ሰላም እና ደኅንነት የሚያውኩ” በማለት የገለጿቸውን ተፈላጊዎች አሳልፎ በመስጠት ላይ አምባሳደሩ ትብብር እንዲያደርጉ መጠየቃቸውንሞ ፌደራል ፖሊስ ጠቅሷል።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ የአሜሪካ ድምፅ የጠየቃቸው፣ በአዲስ አበባ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ማርዦን ካምራኒ በኢሜል በሰጡት ምላሽ፣ አምባሳደሩ እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ግንቦት 2 ቀን ተገናኝተው፣ ከዩናይትድ ስቴትስ የሚሰራጩ ቀስቃሽ ንግግሮች ስለደቀኗቸው ፈተናዎች እና በነዚኹ ተዋናዮች ሊካሔዱ ስለሚችሉ የገቢ ማሰባሰቢያዎች መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ጉዳዩን፣ በሥራ ላይ ካለው ሕግ እና ከሕገ መንግሥታዊ መብት አንጻር እየተመለከተችው እንደኾነች፣ አምባሳደሩ መጠቆማቸውንም ቃል አቀባይዋ አስረድተዋል።

ኤምባሲውም ኾነ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በመግለጫዎቻቸው በስም የጠቀሷቸው ግለሰቦችም ኾነ ሌሎች አካላት የሉም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG