በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር መቐለንና ባሕር ዳርን ጎበኙ


በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አረጋ ከበደ
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አረጋ ከበደ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ፣ ባለፉት ሦስት ቀናት፣ በመቐለ እና በባሕር ዳር ከተሞች ጉብኝት አድርገው፣ ከክልሎቹ ባለሥልጣናት እና የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋራ ተወያይተዋል።

አምባሳደሩ ጉብኝቱን ያደረጉት፣ የአሜሪካ መንግሥት በክልሎቹ የሚያካሒዳቸውን ፕሮግራሞች እና ሌሎች ተግባራትን የበለጠ ለመረዳት እንደኾነ፣ በዐዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል።

አምባሳደሩ በመቐለ ባደረጉት ጉብኝት፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋራ፣ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሒደትንና በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በሚሰፍንበት መንገድ ላይ እንደተወያዩ ታውቋል።

አምባሳደሩ በተጨማሪም፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶር. ፋና አጎንና በአሜሪካ የትምህርት ልውውጥ ፕሮግራም ተጠቃሚ የኾኑ ተወካዮችን አግኝተው፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፣ በትምህርት እና በኢኮኖሚ መስክ እገዛውን በሚያጠናክርበት መንገድ ላይ እንደተወያዩ፣ መግለጫው አስፍሯል። አምባሳደር ማሲንጋ፣ በመቐለ ጉብኝታቸው፣ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት(USAID) የምገባ ፕሮግራም ጣቢያን ጎብኝተዋል።

አምባሳደሩ በባሕር ዳር በነበራቸው ጉብኝትም፣ ከክልሉ ፕሬዚዳንት አረጋ ከበደ እና ከከተማው ከንቲባ ጎሹ እንዳለማኹ፣ እንዲሁም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶር. ፍሬው ተገኝ ጋራ ተወያይተዋል። በውይይታቸውም፣ በዐማራ ክልል ያለው ቀውስ፥ በቁልፍ ተቋማት እና በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ ስላሳደረው ተጽእኖ፣ አምባሳደሩ ከባለሥልጣኑ በቀጥታ መስማታቸው ተገልጿል።

አምባሳደሩ፣ በሁለቱ ከተሞች ያደረጉት ጉብኝት፣ ከሳምንት በፊት በአፋር፣ ሰመራ ያደረጉት ጉብኝት ቀጣይ እንደኾነና ወደፊትም የሕዝቡን ኹኔታ ይበልጥ ለመገንዘብ፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ መግለጫው ጠቁሟል።

ጉብኝቱ፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ ዘላቂ ልማትንና እድገትን ለማምጣት የሚያደርገው ድጋፍ ይበልጥ ውጤታማ እንዲኾን፣ ከአካባቢ አጋሮች እና ተቋማት፣ እንዲሁም ክልላዊ መንግሥታት ጋራ ለመመካከር መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር፣ ከኤምባሲው የተገኘው ጋዜጣዊ መግለጫ አክሎ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG