"ሩሲያ ሱዳን ውስጥ የሚዋጉትን ሁለቱን ወገኖች በገንዘብ ትደግፋለች" ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ትላንት ሰኞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሳታለች፡፡ ይህም ሞስኮ የራሷን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ሁለቱንም ወገኖች ደጋፊያቸው እየመሰለች መጫወት ይዛለች የሚለውን የቀደመውን ዋሽንግተን ድምዳሜ ከፍ ያደረገ ሆኖ ታይቷል፡፡
በሱዳን ጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ መካከል በጎርጎርሳውያኑ ሚያዚያ 2023 የተጀመረው የእርስ በእርስ ጦርነት በዓለም ትልቁን የመፈናቀል እና የረሃብ ቀውስ አስከትሏል።
ባለፈው ኅዳር በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና የሰብአዊ ርዳታ መግባቱን እንዲያረጋግጡ የሚጠይቀውን ረቂቅ ውሳኔ ቀሪዎቹ 14 የምክር ቤት አባላት ሲደግፉት ሩሲያ ድምጽ በመሻር ሥልጣኗ ተጠቅማ ጥላዋለች፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ትላንት ሰኞ ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር "ሩሲያ ማደናቀፍን መርጣለች፡፡ ብቻዋን ቆማ ሲቪሎች እንዲጎዱ ድምጽ ሰጥታለች፡፡ ሁለቱንም ተፋላሚ ወገኖች በገንዘብ ትደግፋለች፡፡ አዎ! ሁለቱንም ወገኖች እያልኩ ነው" ብለዋል።
በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ ልዑክ ቃል አቀባይ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ተጠይቀው፤ ሩሲያ "በሱዳን የወርቅ ንግድ ውስጥ ጥቅም እንዳላት ዋሽንግተንእንደምታውቅ ገልጸው ለተፋላሚዎቹ ወገኖች "በህገወጥ የወርቅ ንግድም ሆነ በጦር መሳሪያ አቅርቦት መልክ የሚደረግ ቁሳዊ ድጋፍ ዩናይትድ ስቴትስ ታወግዛለች" ብለዋል፡፡
በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሩሲያ ምክትል አምባሳደር ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ በሰጡት ምላሽ “ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች የዓለም ኃያላን መንግሥታት ላይ በራሷ መለኪያ ለመፍረድ በመሞከሯ እናዝናለን” ብለዋል።
ሮይተርስ ስለጉዳዩ ከሱዳን ተፋላሚ ወገኞች ወዲያውኑ ለዘገባው ምላሽ ሊያገኝ አለመቻሉን አስታውቋል፡
መድረክ / ፎረም