በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ በኮንጎ ስምንት ሰላም አስከባሪዎችን አገደ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ

ከወሲብ ቅሌት ጋር በተገናኘ የተወነጀሉ ስምንት የሰላም አስከባሪ አባላት ከሥራ ታግደው ምስራቅ ኮንጎ ውስጥ መታሰራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ትናንት ሐሙስ በኒው ዮርክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ የሰላም አስከባሪ ሃይል አባላት፣ በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ አንድ ጣቢያ ላይ እንደነበሩና በእረፍት ሰዓታቸው በወሲብ ግብይት በሚታወቅ መጠጥ ቤት ውስጥ ሲዝናኑ እንደነበር መረጃ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ የተባበሩ መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ወታደራዊ ፖሊሶች፣ የስነምግባር እና የዲሲፕሊን ኃላፊዎች የደረሳቸውን ሪፖርት ለመገምገም ስፍራውን መጎብኘታቸውን ዱጃሪክ ተናግረዋል፡፡

የተወነጀለውን የጦር ክፍል በሚመለከት በከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎችና አዛዞች ዘንድ ከፍተኛ የቁጥጥር ድክመት መኖሩንም ዱጃሪክ ጨምረው ገለጸዋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎች እስኪገኙና ሙሉ ምርመራ እስኪደረግ ድረስ ሰላም አሰከባሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሆነው እንደሚቆዩ ተመልክቷል፡፡

ስለ ጉዳዩ ዝርዝር ሁኔታ ለመናገር ፍቃድ ያልተሰጣቸው አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ ስምንቱ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከደቡብ አፍሪካ የመጡ መሆናቸውን እና በሰሜን ኪቩ ግዛት በቤኒ ከተማ የሰዐት ዕላፊን በመተላለፍ ፈቃድ በሌለው ቡና ቤት ውስጥ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ሳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG