በተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኮንትራት የተያዘና ስንዴ የጫነች አምስተኛ መርከብ ከዩክሬን ጥቁር ባህር ወደብ ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ እያቀናች መሆኑን የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
መርከቧ 30 ሺህ ቶን የዩክሬን ስንዴ ለኢትዮጵያ መጫኗም ታውቋል።
በተመድ ፕሮግራም አማካኝነት ዩክሬን እስከ አሁን 150 ሺህ ቶን ስንዴ ወደ ኢትዮጵያ፣ የመን፣ እና አፍጋኒስታን መላኳ ታውቋል።
የሩሲያን ወረራ ተከትሎ የጥቁር ባህር ወደቦች በመዘጋታቸው ከዩክሬን ወደ ውጪ ገበያ የሚላከው እህል በመቆሙ፣ የእህል ዋጋ ሰማይ ሲነካ፣ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ እጥረት አስከትሏል።
በተመድ መሪነት በተካሄደ ድርድር ሦስት የጥቁር ባህር ወደቦች ባለፈው ሃምሌ መልሰው ሲከፈቱ፣ በዩክሬን የተከማቸው እህል ቀስ በቀስ መውጣት ጀምሯል።