በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቡርኪና ፋሶ ጂሃዲስቶች ሳይፈጽሙት አልቀረም በተባለ ጥቃት 12 ሲቪሎች ተገደሉ


ቡርኪና ፋሶን ከማሊ በሚያዋስነው የሰሜን ምዕራብ ድንበር አካባቢ በጂሃዲስትነት የሚጠረጠሩ ቡድኖች በፈጸሙት ጥቃት 12 ሲቪሎች ተገድለው 6 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ትናንት እሁድ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

በደርዘን የሚቆጠሩ ወንዶች በሞተር ብስኪሌት ላይ በመሆን ሳናካዱጎ የተባለችውን መንደር ባለፈው ሐሙስና ዓርብ አጥቅተዋል ሲሉ አንድ ነዋሪ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል። የሟቾቹ ቁጥር ከተጠቀሰው ሊበልጥ እንደሚችል ተፈርቷል።

አንድ የዓይን እማኝ እንዳሉት መንደሩ ሙሉ ለሙሉ በእሳት የወደመ መሆኑንና ነዋሪዎቹ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ መንደሩን ለቀው እየወጡ መሆኑን ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ መንደራቸውን ሲለቁ ምንም ንብረት እንዳሊያዙና እንስሶቻቸውም በአጥቂዎቹ እንደተዘረፉ የዓይን እማኙ ጨምረው ገልጸዋል።

ያራን በተባለቸው ሌላ ከተማ ትናንት እሁድ ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበርም ታውቋል።

በቦርኪና ፋሶ በጂሃዲስቶች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቅርብ ሳምንታት ውስጥ እየጨመሩ መምጣታቸው ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት ሲቪሎችን ጨምሮ 40 የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሎ ከዛ ቀደም ብሎ በነበረው ሳምንት በጂሃዲስቶች በተከፈተ ጥቃት 50 የሚሆኑ መገደላቸው ታውቋል።

በዓለም እጅግ ደሃ ከሆኑ አገሮች አንዷ የሆነቸው ቡርኪና ፋሶ ከማሊ በሚመጡ ጂሃዲስቶች ጥቃት ሲፈጸምባት ሰንብታለች።

በሺህ የሚቆጠሩ ሲገደሉ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

አርባ በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ነው።

XS
SM
MD
LG