ለዩክሬን የሚሠጡትንም ድጋፍ ይቀጥላሉ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ትናንት በዋይት ሃውስ ባደረጉት ውይይት፣ ሁለቱ አገራት በኃይል ሽግግር እና አዲስ በቀል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንደሚኖራቸው ይፋ አድርገዋል።
ሁለቱ መሪዎች፣ ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመመከት ለምታደርገው ጥረት የሚሰጡትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በወሳኝ እና አዲስ በቀል ባሏቸው የቴክኖሎጂ ዘርፎች፣ በሰው ሰራሽ ልህቀት፣ የኢኮኖሚ ዋስትና እና የዲጂታል ሽግግር፣ እንዲሁም ንጹህ ኃይልን በተመለከተ ሁለቱ አገራት የመሪነት ሚና የሚጫወቱበትን ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፣ ባይደን “የኢኮኖሚ ግንኙነቶቻችንን እንዲሁም የአየር ንብረት ቀውስን በተመለከተ መልካም ውይይት እና ስምምነት ላይ ደርሰናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው “እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ አገራት የእኛን ግልጽነት እና ክፍት መሆን ተጠቅመው የአእምሮ ንብረታችንን ይሰርቃሉ፣ ቴክኖሎጂንም ለመጨቆኛ መሣሪያ ይጠቀማሉ፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም” ብለዋል።
ሱናክ ፓርቲያቸው ከአራት ዓመታት በፊት ቃል በገባው መሠረት ከአሜሪካ ጋር ሁሉን አቀፍ ነጻ የንግድ ስምምነት እንዲያደርጉ በአገራቸው ግፊት ቢገጥማቸውም ሃሳቡ በአሜሪካው ኮንግረስ ድጋፍ አላገኘም።