ኢስታንቡል ውስጥ ደብዛው የጠፋውን የሳዑዲ አረቢያዊውን ጋዜጠኛ ዣማል ኻሾግዢን አስከሬን ለመፈለግ የተሠማሩ የቱርክ ፖሊስ አባላት ዋና ከተማዪቱ አቅራቢያ የሚገኘውን ቤልግራድ ጫካ እያሰሱ መሆናቸውን የሃገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በሌላ በኩል ደግሞ ኻሾግዢ እንዴት እንደተገደለ የሚጠቁም የተቀረፀ ድምፅ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት አስደምጠዋል የተባለውን መረጃ የቱርክ ባለሥልጣናት አስተባብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ሰሞኑን ቱርክን የጎበኙ ጊዜ ያንን የተቀረፀ ድምፅ አዳምጠዋል ሲሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
ፖምፔዮ ወደ ደቡብ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት በሰጡት ቃል ያዩት ምሥልም ይሁን ፅሁፍ ወይም የሰሙት የተቀረፀ ድምፅ አለመኖሩን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚያገኙትን ማንኛውንም የምርመራም ሆነ የፍለጋ ውጤት ለዓለም እንደሚያሳውቁ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ቻቩሾህሉ ለሃገራቸው መንግሥታዊ የዜና አገልግሎት አናዶሉ ዛሬ ገልፀዋል።
ቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል ወደሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ሲገባ እንጂ ሲወጣ ያልታየውና የቨርጂንያ ግዛት ነዋሪ የሆነው የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ኻሾግዢ “ተገድሏል” ብለው ያስቡ እንደሆነ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ ተጠይቀው “ሁኔታዎች የሚያሳዩት በርግጥ ያንን ሁኔታ ነው፤ በጣም ያሳዝናል” ብለዋል።
በግድያው ውስጥ የሳዑዲ አረቢያ እጅ ካለበት “የበረታ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ሲሉ ዝተዋል ትረምፕ።
ዣማል ኻሾግዢን በሳዑዲ አረቢያ የተላኩ ሰዎች ገድለውታል ሲሉ የቱርክ ባለሥልጣናት ያሰሙትን ክሥ ሪያድ እንድታጣራ ጊዜ ለመስጠት የትረምፕ አስተዳደር እንደሚፈልግ ተገልጿል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ