ቱርክ እና ሦሪያ ውስጥ እጅግ ኃይለኛው የመሬት መናወጥ ከናዳቸው ህንጻዎች ፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች በህይወት የማውጣት ተስፋ እየተመናመነ ነው። የሆነ ሆኖ ዛሬም በቱርክ ደቡባዊ ክፍለ ግዛት በርካታ ሰዎችን ለማውጣት መቻሉ ተዘግቧል።
የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞች በነዳጅ ዕጥረት ባለው ከባድ ቅዝቃዜ እና መንገዶች እና ሌላም የመሰረተ ልማት አውታሮች በመፈራረሳቸው የሚንቀሳቀሱት በከባድ ችግር መሆኑ ተጠቁሟል።
የቱርክ እና የሦሪያ አዋሳኝ አካባቢዎችን ባለፈው ሰኞ በመታው ርዕደ መሬት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ21 ሺህ ማለፉን ባለሥልጣናቱ አስታውቀዋል።
በርዕደት መለኪያው መሣሪያ ሪክተር ስኬል ላይ 7 ነጥብ 8 ያስመዘገበው ነውጥ ባጠፋው ህይወት ብዛት እአአ በ2011 ጃፓን ውስጥ 20 ሺህ ሰው ካለቀበት የመሬት መንቀጥቀጥና ሱናሚ ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ተመልክቷል።
በየፍርስራሹ ስር ለተቀበሩ ሰዎች በህይወት ለመድረስ የሚደረገው ጥረት ባለው የመሣሪያ ዕጥረት የተነሳ እየተስተጓጎለ መሆኑ ታውቋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሁለቱም ሀገሮች በመሬት ነውጡ የተጎዱ አምስት መቶ ሺ ሰዎችን መርጃ የ46 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተማጽኗል።
በተያያዘ ዜና ቱርክ "ለበርካታ ዓመታት ጥብቅ የዘመናዊ ግንባታ ደንቦችን ሳታስከብር ቆይታለች ይባስ ብላም ለርዕደ መሬት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የህንጻ ግንባታ እንዲደራ አበረታትታለች" ሲሉ የዘርፉ አዋቂዎች ተናገሩ።
ቱርክ ጉዳዩን ትኩረት እንድትሰጠው የከርሰ ምድር እና የምህንድስና ሙያ ጠበብት ለረጅም ጊዜ ሲያስጠነቅቁ የነበረ ሲሆን ያሁኑን ከባድ ርዕደ መሬት ተከትሎ ብርቱ ትችት እየቀረበባት መሆኑ ተመልክቷል።
በመሬት ነውጡ ቱርክ እና ሦሪያ ውስጥ ብዙ ሺህ ህንጻዎች ፈርሰዋል። አንደኛው የግንባታ ዘርፍ አዋቂ የደረሰው አደጋ መንስዔ የመሬት ነውጡ ሳይሆን ትክክለኛ ያልሆነ የህንጻ ግንባታ እንደሆነ ገልጸዋል።