በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቱርክ በስዊድን የኔቶ አባልነት እና በዩክሬን እህል ስምምነት


የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዘኪ አክቱርክ
የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዘኪ አክቱርክ

የስዊድን የኔቶ አባልነት ጉዳይ፣ በፓርላማው ይኹንታ ላይ የተንጠለጠለ ነው፤ ሲሉ፣ የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናገሩ፡፡

ቃል አቀባዩ ዘኪ አክቱርክ፣ ትላንት ኀሙስ፣ በአንካራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ “በማድሪድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገቡ ቃል ኪዳኖች፣ በተጨባጭ እስከተሟሉ ድረስ፣ የስዊድን አባልነት የማይጸድቅበት ምንም ምክንያት የለም፤ ሀገራችንና ፓርላማችንም በዚኽ ያምናሉ፤” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ይህን የተናገሩት፣ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታዪፕ ኤርዶዋን፣ ስዊድን፥ ወደ ጦር ቃል ኪዳኑ ኅብረት መግባቷን አስመልክቶ ያቀረቡትን ተቃውሞ ተከትሎ ነው፡፡ መግለጫው የተሰጠው፥ ተቃውሞውን ለመመርመር እና እልባት ያጣውን ጉዳይ ለማንቀሳቀስ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ለመምክር የመጡ፣ የስዊድንና የቱርክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ብራሰልስ በሚገኘው የኔቶ ዋና መሥሪያ ቤት ሲደርሱ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

በማድሪድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገቡ ቃል ኪዳኖች፣ በተጨባጭ እስከተሟሉ ድረስ፣ የስዊድን አባልነት የማይጸድቅበት ምንም ምክንያት የለም፤ ሀገራችንና ፓርላማችንም በዚኽ ያምናሉ፤”

ቱርክ እ.ኤ.አ. በ2016፣ መንፈቅለ መንግሥቱን ሞክረዋል፤ ያለቻቸውን አክራሪ የኩርድ ቡድኖችን ጨምሮ፣ ለአንካራ የጸጥታ ስጋት ናቸው፤ ለምትላቸው ቡድኖች፣ በጣም የለዘበ አቋም አላት፤ ስትል ስዊድንን ትከሣለች፡፡

ቃል አቀባዩ አክቱርክ፣ በቅርቡ በስቶክሆልም የተፈጸመውን የቁርኣን ማቃጠል ድርጊት አውግዘዋል፡፡ ድርጊቱንም፣ “አስከፊ ጥቃት” ሲሉ ጠርተውታል።

ባላፈው፣ የኢድ አል አድሃ(አረፋ) በዓል ላይ፣ አንድ የኢራቅ ክርስቲያን ስደተኛ፣ በስዊድን መዲና በሚገኝ አንድ መስጊድ ፊት ለፊት፣ የቅዱስ ቁርአንን መጽሐፍ ማቃጠሉ ይታወሳል፡፡

የስዊድን ፖሊሶች፣ ተቃውሞው፥ “ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ነው፤” በሚል መፍቀዳቸው ተመልክቷል፡፡

ዩክሬን፣ በጥቁር ባሕር ወደቦች በኩል፣ እህል ወደ ውጭ እንድትልክ ስለሚፈቅደውም ስምምነት፣ ቱርክ፥ “ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ስለሚያበቃ ይራዘም ዘንድ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን፣ የሩሲያ ፌዴሬሽንንና የዩክሬናውያን ባለሥልጣናትን እያነጋገረች ነው፤” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG