የቱርክ እና ኢራን መሪዎች የሶሪያው ፕሬዝደነት ባሻር አል አሳድ ሥልጣን ካከተመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ካይሮ ላይ በመካሄድ ላይ ባለውና በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የስምንት ሀገራት ጉባኤ ላይ ተገናኝተዋል።
በሶሪያው ጦርነት ሁለቱ ሀገራት በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው የነበረ ሲሆን፣ ቱርክ የአሳድ ተቃዋሚዎችን ስትደግፍ ኢራን ደግሞ የአሳድን አገዛዝ ደግፋለች።
በሶሪያ መረጋጋትና ሰላም እንዲሰፍን፣ ሽብርተኝነት እንዲጠፋ እንዲሁም የተረጋጋችና ፀጥታ የሰፈነባትን ሶሪያ ማየት እንደሚሹ የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሽፕ ታይፕ ኤርዶዋን በውይይታቸው ወቅት ማስታወቃቸውን የቱርክ ፕሬዝደንታዊ ጽሕፈት ቤት በአወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል። የሶሪያን የግዛት ሉአላዊነት እና የሀገሪቱን አንድነት መጠበቅ አስፈላጊ እንደኾነም ኤርዶዋን መናገራቸውን ጽሕፈት ቤቱ አመልክቷል።
ከኢራኑ ፕሬዝደንት ማሱድ ፐዘሽካን ቢሮ የወጣው መግለጫ በበኩሉ፣ የሶሪያ ድንበር ሳይደፈር ተጠብቆ የመቆየቱ አስፍላጊነት ላይ ፕሬዝደንቱ አጽንኦት መስጠታቸውን አመልክቷል።
እስራኤል በቀጠናው ፈጽማዋለች ያሉትንና “ወንጀል” ሲሉ ለገለጹት ድርጊት ሙስሊም ሀገራት ኃላፊነት ባለው መንገድ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ፕሬዝደንቱ ማሳሰባቸውም ተጠቁሟል።
“ግጭት በሚካሄድባቸው ሥፍራዎች የሚገኙ ሰዎች ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከል ሃይማኖታዊ፣ ሕጋዊ እና ሰብአዊ ግዴታችን ነው” ሲሉም ማሱድ ፐዘሽካን ማከላቸውን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
‘ዲ 8’ በሚል የሚጠራው የስምንት ሃገራት የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ በካይሮ በመካሄድ ላይ ያለው፣ በጋዛ ጦርነት በሚካሄድበት፣ በሌባኖስ በጽኑ ያልተከበረ የተኩስ ማቆም ስምምነት ባለበት፣ ሶሪያ ባልተረጋጋችበትና ቀጠናው በአጠቃላይ በግጭት በሚተራመስበት ወቅት ነው።
መድረክ / ፎረም