የዩክሬን ስንዴ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ የባህር መውጫ መክፈት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ ከቱርክ አቻቸው ጋር አንካራ ውስጥ ተገናኝተው ተናጋግረዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱም ወገኖች በዓለም ዙሪያ የተከሰተውን የምግብ ቀውስ ሊያስወግድ የሚያስችል ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ተገልጿል።
ሁለቱ ባለሥልጣናት ትናንት፤ ረቡዕ በጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የቱርኩ ሜቭሉጥ ቻቩሾህሉ የዩክሬን መርከቦች የስንዴ ምርት ለዓለም ገበያ ማቀረብ የምኒችሉበት ደኅንነቱ የተጠበቀ የባህር መተላለፊያ እንዲከፈት ሃገራቸው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር እንደምትሠራ ገልፀዋል።
ቱርክ ዕቅዱን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አድርጋ እንደምትመለከት የጠቆሙት ቻቩሾህሉ ይሁን እንጂ ሩሲያና ዩክሬን ከመንግሥታቱ ድርጅት የሚቀርብላቸውን ጥያቄ መቀበል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
“ቱርክ ዝርዝሩ ላይ ለመነጋገር የሚያስችለውን ስብሰባ ኢንስታቡል ላይ ልታዘጋጅ ትችላለች" ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
የሩሲያው ላቭሮቭ ግን “ችግሩን ለማስወገድና የዩክሬን መርከቦች በወደቡ በኩል እንዲያልፉ ለማድረግ ዩክሬናዊያኑ በወደቦቻቸው ዙሪያ የቀበሯቸውን ፈንጂዎ ማንሳት ወይም ለመርከቦቻቸው መውጫ ክፍት መንገዶችን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል” ሲሉ አገራቸው ብቸኛ መፍትሄ ብላ የምታምነውን ተናግረዋል።
ዩክሬን በበኩሏ ደግሞ ከሩሲያ ጥቃት ለመከላከል በሚል በወደቦቿ ዙሪያ የቀበረቻቸውን ፈንጂዎች ለማንሳት ሩሲያ በተከፈተው ቀዳዳ ገብታ ጥቃት እንደማትፈፅም ዋስትና እንድትሰጣት ትፈልጋለች።
በዓለም ዙሪያ የስንዴ ገበያ እጅግ የተወደደ ቢሆንም ዩክሬን ውስጥ በሚሊዮኖች ቶኖች የሚቆጠር ስንዴ መውጫ አጥቶ መቀመጡ ተገልጿል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት ግን የናረው የምግብ ዋጋ ከዩክሬኑ ጦርነት ጋር የሚያገናኘው ነገር በጣም አነስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።