የቱኒዚያ ባለሥልጣናት ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ህገወጥ ፍልሰተኞች የሚጠቀሙበትን ጀልባ በመስራት የተጠረጠረውን የ45 ዓመቱን ጣሊያናዊ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ዛሬ ረቡዕ አስታወቁ፡፡
ግለሰቡ በጀልባ ግንባታ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠራ መሆኑን በምስራቅ ቱኒዝያ የምትገኘው የሞናስቲር ከተማ አቃቤ ህግ ቃል አቀባይ ፋሪድ ጃሃ ተናግረዋል።
ከሜዲትሬኒያን ባህር ወደ አውሮፓ እንዲያሻግር ከፕላስቲክ የተሰራውን ጀልባ ግንባታ በማቀድ የተሳተፉ ሶስት ቱኒዚያውያንም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልከቷል፡፡ በየዓመቱ ከቱኒዚያ እና ሊቢያ በኩል የሚወጡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ጣሊያን ዋና መዳረሻቸው መሆኗ ተዘግቧል፡፡
ከህገወጥ የፍልስተኞች ጉዳይ ጋር በተያያዘ አንድ የአውሮፓ ዜጋ በቱኒዝያ ሲታሰር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ህገ ወጥ ጀልባዎች ብዙ ጊዜ በአካባቢው በሚገኙ ቱኒዚያውያንና ከሰሃራ በታች ባሉ ህገወጥ የሰዎች አስተላላፊዎች የሚሰሩ ናቸው፡፡
እኤአ ከጥር 1 ጀምሮ ቢያንስ 103 ጊዜያዊ ጀልባዎች በቱኒዚያ የባህር ጠረፍ ላይ ተገልብጠው 341 አስከሬኖች ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህ አብዛኞቹ የውጭ ዜጎች መሆናቸውን የቱኒዚያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ የጀልባ አደጋ ከ1,300 በላይ ሰዎች ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ሲል አንድ የቱኒዚያ የመብት ተሟጋች ቡድን ገልጿል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደዘገበው ከጀልባው አደጋ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት የሞቱትን ከ3,000 በላይ ፍልስተኞችን ጨምሮ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከ27,000 በላይ ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም