ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመዋጋት የአሜሪካንን ድጋፍ መልሳ ለማግኘት እየጣረች ባለችበት ወቅት፣ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮለድሚር ዜለንስኪ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋራ ዛሬ ዐርብ ተገናኝተው ወሳኝ በኾኑ ማዕድናት ዙሪያ ስምምነት እንደሚፈራረሙ ተገልጿል።
በቅርብ ቀናት ውስጥ በተደረጉ ድርድሮች የተደረሰው የማዕድን ስምምነት፣ የዩክሬንን ሰፊ የማዕድን ሀብት ለዩናይትድ ስቴትስ ክፍት የሚያደርግ ቢኾንም፣ አሜሪካ ለዩክሬን የደኅንነት ዋስትና ማረጋገጫ ባለመስጠቷ ዩክሬንን ቅር አሰኝቷል።
ስምምነቱ ዩናይትድ ስቴትስ ለኪቭ የጦር መሳሪያ አቅርቦት ያወጣችውን በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ለማስመለስ ያስችላታል ተብሏል።
ስልታዊ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል ባለፈው ዓመት ባጠናው ጥናት ግን የዩናይትድ ስቴትስ ምክርቤት ለዩክሬን ከመደበው ገንዘብ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ገንዘብ ወጪ የተደረገው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መኾኑን አመልክቷል።
ያለፉትን ሳምንታት የዩክሬን ፕሬዝደንት ጋራ በርቀት ሲነጋገሩ የሰነበቱት ትራምፕ፣ ዜለንስኪ ጦርነቱን ያስተናገዱበትን መንገድ በመተቸት አምባገነን ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን፣ የማዕድን ስምምነቱን እንዲቀበሉ አሳስበዋቸው ነበር።
ሆኖም ትራምፕ ከእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ጋራ በሰጡት መግለጫ "እኔ ይሄን ብያለሁ? እንደዛ ማለቴን ማመን ያቅተኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ ከዜለንስኪ ጋራ ተገናኝቶ መወያየትን በጉጉት የሚጠብቁት ጉዳይ መኾኑን ገልጸው፣ የዩክሬንን ጦርም በጀግንነት አወድሰዋል
ትረምፕ አክለውም፣ "ጦርነቱ እንዲቆም በጣም ጠንክረን እየሥራን ነው። በዚኽም ብዙ መሻሻሎችን አድርገናል። ኺደቱም በፍጥነት እየተከናወነ ይመስለኛል" ብለዋል።
መድረክ / ፎረም