ዩናይትድ ስቴትስ የቨርጂንያዪቱ ሻርለትስቪል ከተማ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ የተነሣውን የሕይወት መጥፋት ያስከተለ ሁከት የጫሩትን ኔኦ ናዚዎችና የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ አራማጅ የሆኑትን ኩ ክለክስ ክላን የሚባል ቡድን አባላት “ወንጀለኞችና ወንበዴዎች” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አውግዘዋቸዋል።
እጅግ ከበዛ ግፊት በኋላም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ እንዲህ የሁከተኞቹን ስም ጠርተው ቢያወግዙም “ዘገዩ” በሚል የተነሣባቸው ወቀሣና ቁጣ የበረደ አይመስልም።
በሌላ በኩል ደግሞ ሻርለትስቪል ላይ የተካሄደውን የቅዳሜውን የነጭ ብሄረተኞች ሰልፍ እንደሚያወግዝና እንዲህ ዓይነቶቹን ለጥቃት የሚጋበዙ ፅንፈኛ ቀኝ ሃሣቦችን በሰላማዊ መንገድ ከሚቃወሙ ጎን እንደሚቆም የጀርመን መንግሥት አስታውቋል።
ሻርለትስቪል ከተማ ውስጥ የተጠራሩት ‘ነጭ የበላይ ነው’ ባዮች፣ ኔኦ ናዚና በጥቁሮችና በአይሁድ ላይ ባላቸው የበረታ ንቀትና ጥላቻ ተመሳስለው ዘረኞቹ የታደሙበት ቡድን ኩክለክስ ክላን (በምኅፃር ኬኬኬ ይባላል) አባላት የጠሩትን ስብሰባ ተቃውመው በወጡ ፀረ-ዘረኝነት አስተሳሰብ ያላቸው ሌሎች ሰልፈኞች ላይ አንድ የመጀመሪያዎቹ አባል መኪና ነድቶባቸው አንዱት ሴት ገድሏል።
ይህ ወንጀል የተፈፀመው በሁለቱ ተፃራሪ ሰልፈኞች መካከል ሙሉውን ረፋድ የዘለቀ መቆራቆስና ትርምስ ከተካሄደ በኋላ ነው።
ይህ የሻርለትስቪል አጋጣሚና ትራዠዲ ‘በመናገር ወይም ሃሣብንና እምነትን በመግለፅ ነፃነትና በጥላቻና በፀብ ወንጀሎች መካከል ወሰኑ ያለው የት ነው?’ የሚል የተጋጋለ ውይይት አጭሯል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ‘እጅግ ዘገዩ’ የተባሉባቸውን ቃላት ሁለት ቀናት አሳልፈው ትናንት ተንፍሰዋል።
“ዘረኝነት ክፉ ነው። እርሱን አንግበው ሁከትን የሚፈጥሩ ሁሉ፤ ኬኬኬን፣ ኔኦ ናዚዎችንና የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ አራማጆችን፣ እንዲሁም ሌሎችም እኛ እንደአሜሪካዊያን ብርቃችን አድርገን የያዝነው ሁሉ የሚያጥወለውላቸው የጥላቻ ቡድኖች ወንጀለኞችና ወንበዴዎች ናቸው” ብለዋል ትረምፕ።
ምንም እንኳ ትረምፕ ተገፍተውም ቢሆን፣ ሁለት ቀናትን አሳልፈውም ቢሆን ውግዘት ቢያሰሙም ከወቃሾቻቸው የሚወርድባቸውን ቁጣ ለማለዘብ ወይም ለማብረድ የቻሉ አይመስልም።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ