የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ የዩክሬይን ጦርነት እንዲቆም ከሀገሪቱ መሪ ጋራ በአስቸኳይ ድርድር እንዲጀመር በቴሌፎን ካነጋገሯቸው ከሩሲያ መሪ ቭላዲሚር ፑቲን ጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናገሩ።
ትረምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ መገናኛቸው ላይ በአወጡት ጹሑፍ "ለዩክሬን ፕሬዝደንት ዜለንስኪ ስላደረግነው ውይይት ስልክ ደውለን በመንገር እንጀምራለን። አሁን እሱን ላደርግ ነው " ብለዋል። አስከትለውም ፕሬዝደንቱ "የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ፥ የሲአይኤ ድሬክተር ጃን ራትክሊፍ፥ እና የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ማይክል ዎልዝ እንዲሁም አምባሳደር እና ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮቭ ድርድሮቹን እንዲመሩ ጠይቄአቸዋለሁ፥ እንደሚሳካም በጣም አምናለሁ" ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው የመደራደሪያ ነጥቦቹን አልዘረዘሩም። ሆኖም በዩክሬይን መከላከያ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደጀርመን የተጓዙት የመከላከያ ሚንስትር ፒት ሄግሴት ዛሬ ረቡዕ በሰጡት ቃል ዩክሬን የምታነሳው ቁልፍ ጥያቄ ማለትም የኔቶ አባል የመሆኗ ጉዳይ የመደራደሪያ ነጥብ እንደማይሆን አስታውቀዋል።
"ዩናይትድ ስቴትስ የዩክሬን የኔቶ አባልነት በድርድር የሚመጣው ስምምነት ተጨባጭ ውጤት ይሆናል የሚል ዕምነት የላትም" ብለዋል የመከላከያ ሚንስትር ሄግሴት።
አሜሪካዊው መምህር ማርክ ፎግል ትላንት ማክሰኞ ምሽት ከሩሲያ እሥር ቤት መለቀቃቸውን ተከትሎ የፕሬዝደንት ትረምፕ ዋና የታጋቾች ጉዳይ ተደራዳሪ ስቲቭ ዊትኮቭ ትረምፕ ከሩሲያ መሪ እና ከሳውዲ አረቢያ ልዑል ጋር ያላቸው "ታላቅ ወዳጅነት" ለመምህሩ መለቀቅ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
መድረክ / ፎረም