በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፕሬዚዳንት ትረምፕ የመጀመሪያ ጉብኝት


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን ሰሞኑን ሊያደርጉ እየተዘጋጁ ናቸው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን ሰሞኑን ሊያደርጉ እየተዘጋጁ ናቸው፡፡

ይህ የፕሬዚዳንቱ የመጀመሪያ የውጭ ጉዞ የሚደረገው "አብርሃማዊ" የሚባሉት እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች ምንጭና መቀመጫ ወደሆኑ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገሮች ነው፡፡

ትረምፕ በዚህ ለዘጠኝ ቀናት ይዘልቃል በተባለ ሳዑዲ አረቢያ ላይ የሚጀመር ጉብኝት የአካባቢውን ጉዳይ ከእርሣቸው ከቀደሙት ፕሬዚዳንት ፍፁም የተለየ በተባለ አያያዝ ሊመሠርቱ ማሰባቸውን እንደሚጠቁም ተዘግቧል፡፡

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የመጀመሪያ የውጭ ጉዞ የመጀመሪያ ማረፊያ ሳዑዲ አረቢያ መሆኗ ምናልባት አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት በኢራን ላይ የተጠናከረ ጥምረትን ለመመሥረት የሚያስችል የሱኒ ሙስሊሞች ወገናዊነትን ለመሸመት የታሰበ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡

ትረምፕ ባለፈው ዓመት የምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት በሳዑዲ አረቢያ ላይ ብርቱ ነቀፋና ውረፋን ሲያሰሙ ነበር የሚስተዋሉት፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከተመረጡ ሙስሊሞች ለተወሰነ ጊዜ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ እንደሚያደርጉ በየአጋጣሚው ሲያነሷቸው የነበሩ ዛቻዎችና ከተመረጡ በኋላ ደግሞ አብዛኛ ዜጎቻቸው ሙስሊም ከሆኑባቸው ስድስት ሃገሮች የሚነሱ መንገደኞች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ያወጡት የጉዞ እገዳ ፕሬዚዳንቱ «ሙስሊም ጠል» ናቸው የሚል ክሥና ወቀሳ አስነስቶባቸው ቆይቷል፡፡

ወጣም ወረዳ አሁን ፕሬዚዳንት ትረምፕ የዚህ ታሪካዊነት ያለው የመጀመሪያ ጉዟቸው የመጀመሪያ ማሪፊያ ሪያድ ትሆን ዘንድ መርጠዋል፤ ወስነዋልም፡፡ ለምን? «ሳዑዲ አረቢያ በእሥልምና ሃይማኖት እጅግ ቅዱሳን የሆኑ ሁለት ሥፍራዎች መገኛ ነች፡፡ ፅንፈኝነትን፣ ሽብርተኝነትንና ሁከትን ለመፋለም ከሙስሊም ወዳጆቻችን ጋር የትብብርና የመተጋገዝ ግንባታ አዲስ መሠረት የምንጥለውም እዚያው ነው» በራሳቸው በፕሬዚዳንቱ ቃላት፡፡

ይህ አካሄድ ለትረምፕ ያንን እራሳቸው በራሳቸው ላይ የፈጠሩትን «ፀረ-ሙስሊም» ገፅታ ለማስተካከል የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትረምፕ በርያድ ቆይታቸው ወቅት በአመዛኙ የሱኒ ዘርፍ ተከታይ ከሆኑ ሃያ ሙስሊም ሃገሮች ነገሥታት፣ ኤሚሮችና ርዕሣነ-ብሄር ጋር ይገናኛሉ፡፡

መልዕክታቸው ግልፅ ነው፡- በአካባቢው እጅግ ጠበኛ ነው ሚሉትን የቴህራን መንግሥት ለመጋፈጥ ዩናይትድ ስቴትስ አብራቸው ትሰለፋለች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ኸርበርት ማክማስተር ስለ ፕሬዚዳንቱ ትረምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ሲናገሩ «ሰላምን ለማጠናከር፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመላ ሙስሊም ዓለምና ከዚያም ባሻገር ብዙ መከራን ያደረሰ ቀውስና ሁከትን የሚያመርቱና የሚዘሩትን ከአይሲስ እስከ አል-ቃይዳ እስከ ኢራን እስከ አሳድ አገዛዝ ያሉትን ለመፋለም የሚያስችሉ ደፋርና አዳዲስ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አረብና ሙስሊም አጋሮቻችንን ያበረታታሉ» ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ፕሬዚዳንት ትረምፕ እንደ ግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ ኤል-ሲሲና እንደ ቱርኩ መሪ ረሴፕ ጣዪፕ ኤርዶዋን የመሳሰሉ አምባገነኖችን እየተቀበሉ ያነጋግራሉ ሲሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቶች እሮሮ እያሰሙባቸው ነው፡፡

ይህ የትረምፕ አካሄድ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ብዙ ወቀሣ ከሚሰማባቸው ሱኒ መሪዎች እራሳቸውን ካራቁት ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አካሄድ ፍፁም የተለየ እንደሆነ ታዛቢዎች እየተናገሩ ነው፡፡

ሚስተር ትረምፕ ከርያድ ቆይታቸው በኋላ ወደ እሥራኤልና ወደ ቫቲካን ይጓዛሉ፡፡ ሦስቱ ሥፍራዎች በአንድ አምላክ የሚያምኑት የሦስቱ ታላላቅ አብርሃማዊ ሐይማኖቶች የአይሁድ፣ የክርስትናና የእሥልምና ማዕከሎች ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ትረምፕ በዚሁ የውጭ ቆይታቸው ወቅት ብረስልስ - ቤልጅግ ላይ በሚቀመጠው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ትብብር ድርጅቱ - ኔቶ እና በጣልያኗ የሲቺሉ ታኦርሚና ከተማ በሚደረገው ጂ-ሰቨን ወይም ቡድን ሰባት በሚባሉት በሰባቱ ባለጠጋ ሃገሮች ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ፡፡

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የፕሬዚዳንት ትረምፕ የመጀመሪያ ጉብኝት
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:50 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG