ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለወሲባዊ ፊልም ተዋናይቱ ከተከፈለ የአፍ ማዘጊያ ገንዘብ ጋራ ተያይዞ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ የተከፈተው የክስ ሂደት ዛሬም ቀጥሏል።
በዛሬው የችሎቱ ውሎ የትረምፕ ጠበቃ ችሎት ደንበኛቸው 'እንደ አውሮፓያን የዘመን አቆጣጠር በ2016 ዓ.ም ለዋይት ሃውስ ባበቃቸው ምርጫ ላይ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ተጽዕኖ ለማሳደር ሞክረዋል’ በሚል ከቀረቡባቸው ከ34ቱም ክሶች ነጻ ሊባሉ እንደሚገባ በችሎቱ ለተሰየሙት አስራ ሁለት ከህዝብ የተመረጡ ዳኞች ተናግረዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጠበቃ ቶድ ብላንች ‘ትረምፕ የተከፈተባቸውን አንዱንም ወንጀል አልፈጸሙም፤ አቃቤ ሕጉም ማስረጃ ሊያቀርቡ አልቻሉም’ ብለዋል። አስከትለውም በአቃቤ ሕግ ዋና ምስክር ማይክል ኮኸን ላይ በማነጣጠር ‘ኮኽን የሰጡት የምስክርነት ቃል የሃሰት ነው’ ሲሉ ተከራክረዋል። ትራምፕ የቀረቡባቸውን ክሶች በተደጋጋሚ ማስተባበላቸውን ጠበቃቸው ጨምረው ተናግረዋል።
ነገ ረቡዕ ጠዋት የኒው ዮርኩ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሁዋን መርሻን ከህዝብ ለተውጣጡት ዳኞች የሕግ መመሪያ ከሰጡ በኋላ ክሱን በዝግ ችሎት እንዲመክሩበት ያስረክቧቸዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መሰረት ክህዝብ የተውጣጡት ዳኞች በ77 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝደንት ላይ የጥፋተኝነትም ሆነ ‘ከወንጀል ነጻ’ የሚል ውሳኔ በሙሉ ድምጽ መስጠት አለባቸው። ያ ካልሆነ ግን አቃቤ ሕግ ክሱን እንደገና መክፈት ወይም አለመክፈት በሚለው ላይ ይወስናል።
መድረክ / ፎረም