በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትረምፕ የመከላከያ ዕጩ ፒት ሄግሴት ሹመታቸውን ለማስጸደቅ እየታገሉ መኾናቸውን ተናገሩ


የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ለመከላከያ ሚኒስትርነት የመረጧቸው ፒት ሄግሴት
የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ለመከላከያ ሚኒስትርነት የመረጧቸው ፒት ሄግሴት

የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ለመከላከያ ሚኒስትርነት የመረጧቸው ፒት ሄግሴት፣ ሹመታቸውን የሕግ መወሰኛ ምክርቤቱ እንዲያጸድቅላቸው መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ትላንት ረቡዕ ተናገሩ፡፡ ሆኖም ትረምፕ ለቦታው ሌላ ሰው ለመምረጥ እያሰቡ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች እየወጡ ነው፡፡

የአርባ አራት ዓመቱ የቀድሞው የጦር መኮንን እና የፎክስ ኒውስ የውይይት አቅራቢ ሄግሴት ሹመታቸው በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት መጽደቅ ያለበት ሲሆን "ጾታዊ ጥቃት ፈጽመዋል እንዲሁም ካለመጠን ይጠጣሉ" ከሚሉ ውንጀላዎች ጋራ በተያያዘ ጥያቄዎች እንደሚጠብቋቸው ተገልጿል፡፡

ሄግሴት በወታደራዊም ኾነ በንግድ ዘርፍ ትልልቅ ድርጅቶችን የመምራት ምንም ዓይነት ልምድ የላቸውም፡፡ በመኾኑም በዓለም ዙሪያ ያለውን 2.9 ሚሊዮን የሚደርስ በሥራ ላይ ያለና ተጠባባቂ ሠራዊት እንዲሁም 700 ሺሕ ሲቪል ሠራተኞች የያዘ ተቋም እንዲመሩ መመረጣቸው ያልተለመደ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

በርካታ የአሜሪካ ዜና ማሰራጫዎች ትረምፕ ለቦታው ሌላ ሰው ሊያጩ እያሰቡ መኾናቸውን ዘግበዋል፡፡ ምናልባትም የፍሎሪዳው ሃገረ ገዥ ሮን ዲሳንተስን ወይም የቀድሞዋን የጦር መኮንን የአይዋ ሴኔተር ጆኒ አርነስትን በዕጩነት ያቀርቡ ይሆናል ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ ሄግሴት ሹመታቸውን ለማስጸደቅ ከመታገል ወደኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል፡፡

ትረምፕ በሄግሴት ምትክ ይመርጧቸው ይሆናል የተባሉት የፍሎሪዳው አገረ ገዥ ዲሳንትስ የባሕር ኅይል አባል የነበሩ ሲሆኑ በዘንድሮው ምርጫ ለሪፐብሊካን ፓርቲው ፕሬዝደንታዊ ዕጩነት የትረምፕ ተቀናቃኝ ኾነው ቀርበው ሳይሳካላቸው ቀርቶ ከፉክክሩ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG