ይህ እርምጃ “አሜሪካ ትቅደም” የሚለውን መርኃቸውን ለማስፈፀም እወስዳቸዋለሁ የሚሏቸው ተከታታይ እርምጃዎች አካል መሆኑም ተገልጿል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ትናንት፤ ሰኞ ዩትዩብ ላይ ባወጡት የቪድዮ መልዕክት ፓሲፊክ አቋራጭ የሽርክና ስምምቱን ለዩናይትድ ስቴትስ “አውዳሚ አደጋን የሰነቀ” ሲሉ ጠርተውት “በምትኩ ሥራና ኢንዱስትሪን ወደ አሜሪካ ምድር የሚያመጡ ፍትሐዊ የሁለት ወገን የንግድ ድርድሮችን እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
በአፅኅሮች “ቲፒፒ” እየተባለ የሚጠራው የፓሲፊክ አቋራጭ አጋርነት ውል አባል ሃገሮች ስምምነቱን የፈረሙት ባለፈው የካቲት 2008 ዓ.ም ሲሆን ግባቸው የጋራ ብልፅግናን ማጠናከር፣ ሥራዎችን መፍጠር፣ ለሁሉም አባል ሃገሮች ዘላቂ የምጣኔ ኃብት ልማትን ማበረታታት” እንደሆነ ሠነዱ ይናገራል፡፡
“ስምምነቱ ያለ ዩናይትድ ስቴትስ ተሣትፎ ሙሉ በሙሉ እንደሞተ የሚቆጠር ነው” ሲሉ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ዛሬ ሃሣባቸውን አሰምተዋል፡፡
“አሥራ ሁለቱ አባል ሃገሮች በተገናኙበት ስብሰባ ላይ የፓሲፊክ አቋራጭ ሽርክና ውልን ያለ ዩናይትድ ስቴትስ የማስቀጠል ውይይት ጨርሶ አልተደረገም፡፡ ቲፒፒ ያለ ዩናይትድ ስቴትስ ትርጉም የለሽ ነው፡፡ የጥቅሞችን መሠረታዊ ሚዛን ስለሚያዛባ እንደገና መደራደርም የማይቻል ነው፡፡ የመጭውን የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ፖሊሲዎች በተመለከተ አሁን አስተያየት ከመስጠት መቆጠብን እመርጣለሁ” ብለዋል ሺንዞ አቤ፡፡
ምንም እንኳ ውሉን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቢደግፉትም የተወካዮች ምክር ቤቱ ግን ዩናይትድ ስቴትስ የሕጓ አካል ታደርገውና ትቀላቀለው ዘንድ አልፈቀደም፤ አላፀደቀውምም፡፡
በሌላ በኩል ግን “የትራምፕ ተቃውሞ ስምምነቱን ጨርሶውኑ ሊገድለው አይችልም” ሲሉ የአውስትራሊያ የንግድ ሚኒስትር ስቲቭ ቾዬቦ እየሞገቱ ነው፡፡
ቲፒፒ ተግባራዊ እንዲደረግ የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ ለራሱ የሃገር ውስጥ ጉዳይ እንዲያፀድቀው የሚገባ መሆኑ ቢደነገግም ያ እንዲከናወን ግን የሃያ አራት ወራት ጊዜ እንደሚጠይቅ ሚኒስትሩ ጠቁመው ስምምነቱ ከተፈረመ ያለፈው ጊዜ ግን ገና ስምንትና ዘጠኝ ወራት ብቻ በመሆኑ በቂ ጊዜ ወደፊት መኖሩን አመልክተዋል፡፡
ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲደረግ የአባል ሃገሮችን አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት ወይም ጂዲፒ ሰማንያ አምስት ከመቶ የሚሸፍኑ ሃገሮች ማፅደቅ እንደሚጠበቅባቸው በውሉ ላይ የተደነገገ በመሆኑና የዩናይትድ ስቴትስ ጂዲፒ ብቻውን ስድሣ ከመቶውን የሚይዝ በመሆኑ ያለ ዩናይትድ ስቴትስ ውሉ የሞተ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡
የኦባማ አስተዳደር ቲፒፒን ሲደግፍና ለተግባራዊነቱም ሲታገል የቆየው ለዩናይትድ ስቴትስ ሠራተኛ ኃይል ጥቅም ያስገኛል፤ ውሉ አዳዲስ የደመወዝ፣ የሰዓትና የተሻለ የሥራ ሁኔታን አካትቷል በሚልና ሕፃናት በሥራ ላይ እንዳይሠማሩም ስለሚከለክል እንደሆመሆነ ሲናገር ቆይቷል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡