በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትራምፕ ካቢኔና ተጓዳኝ ጉዳዮች


ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ
ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጭ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሣምንት ውስጥ ቀሪ የካቢኔ አባሎቻቸውን እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል፡፡

ትራምፕ ሰኞ፤ ኅዳር 26/2009 ዓ.ም. የአስተዳደራቸውን የቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስትር ሰይመዋል።

እየገፋና እስካሁን ሳይታወቅ የቀረው ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱ ወደማን እንደሚሄድ ነው።

በሌላ በኩል ግን የዚህ ዓመቱ የግሪን ፓርቲ (የአረንጓዴ ፓርቲ) ተወዳዳሪዋ ጂል ስታይን ኒው ዮርክ ውስጥ የማንሃታን ክፍለ-ከተማ ነዋሪዎችን እየመሩ በሦስት ግዛቶች ውስጥ የድምፅ ቆጠራ በድጋሚ እንዲካሄድ ቅስቀሳ እያደረጉ ናቸው።

በቀዝቃዛው የሰኞ ማለዳ አየር ከትራምፕ ህንፃ ወጣ ብሎ ከፍተኛ ፉክክር በታየባቸው ሦስት ግዛቶች የድምፅ ቆጠራው እንደገና እንዲሠራ የሚጠይቁ ሰልፈኞች መፈክር ሲሰሙ አርፍደዋል፡፡

“እዚህ የተገኘንው ዶናልድ ትራምፕ አንዳችም የሚያስፈራቸው ነገር እንደሌለ ልናረጋግጥላቸው ነው። በዴሞክራሲ ካመኑ፣ ባገኙት ድል ትክክለኛነት ከተማመኑ፤ ቁጣዎን ትተው ረጋ፣ ሰከን ይበሉ” ብለዋል ዶ/ር ስታይን ለዶናልድ ትራምፕ ይድረስ ባሉት መልዕክት።

ይህንን ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ ነገር የሚደግፉም የማይደግፉም አሜሪካዊያን መራጮች አሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገሪቱን ቀጣይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የመሰየም ሥራ ትራምፕ ህንፃ ውስጥ ቀጥሏል። እናም ተመራጭ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ካሏቸው ዝርዝሮች ውስጥ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያጯቸውን በቻይና የቀድሞው የዩናየትድ ስቴትስ አምባሳደር ጆን ሃንትስማንን ጨምሮ ዝርዝሮችን ይፋ እያደረጉ ናቸው።

ይህ ምርጫ ግን በተለይም ሰሞኑን ያነጋገረውና ትራምፕ በቅርቡ ከታይዋን ፕሬዚደንት ጋር ካደረጉት የእንኳን ደስ ያለዎ የስልክ ውይይት አኳያ ትልቅ እርምጃ መሆኑ እየተነገረ ነው። ለምን; ቢሉ፣ የሁለቱ የስልክ ውይይት ለቻይናና ለአሜሪካ ግንኙነቶች፣ «ስጋት ደቃኝ ነው» በመባሉ!

ሌሎች የሚካሄዱና መሞላት ያለባቸው የካቢኔ ቦታዎች እንደ የአገር ውስጥ ጉዳዮች፣ የኢነርጂ፣ የግብርና፣ የአርበኞች ጉዳዮችና የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተራቸውን እየጠበቁ ናቸው።

ትራምፕ የነርቭና የአንጎል ቀዶ ህክምና ዶክተሩንና በዚህ በተጠናቀቀው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካን ፓርቲውን በዕጩነት ለመወከል ተወዳድረው የነበሩትን ቤን ካርሰንን ለቤቶችና ለከተማ ልማት ሚኒስትርነት ሰይመዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት ደኅንነት የሚሟገቱት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት አል ጎር ከዶናልድ ትራምፕና ከሴት ልጃቸው ኢቫንካ ጋር ተገናኘው ነበር፡፡ “ለመልካም የጋራ ግንኙነት የተካሄደ ሀቀኛ ውይይት” ብለውታል ጎር ከተመራጩ ፕሬዚዳንት ጋር ያደረጉትን ንግግር። እንደተደሰቱበት የገለፁት ውይይታቸው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ “የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የቻይና ማደናገሪያ ነው” ብለው ቢያምኑም አቋማቸውን ዳግም ለመመርመር ፈቃደኛ እንደሆኑ ግን ባለፈው ሳምት ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጠቁመዋል።

ለሙሉው ዘገባ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

የትራምፕ ካቢኔና ተጓዳኝ ጉዳዮች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:12 0:00

XS
SM
MD
LG