በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ የጣሉትን ቀረጥ ተከትሎ ሜክሲኮ፡ ካናዳ እና ቻይና የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ አስጠነቀቁ


የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ፤ ኦትዋ፤ እአአ የካቲት 4/2025
የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ፤ ኦትዋ፤ እአአ የካቲት 4/2025

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ አዲስ ቀረጥ መጣላቸውን ተከትሎ ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይናም በየበኩላቸው የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ አስጠነቀቁ።

ዩናይትድ ስቴትስ ሁለቱ ዋና ዋና የንግድ ሸሪኮቿ ሜክሲኮ እና ካናዳ በሚልኳቸው ምርቶች ላይ የጣለችው አዲስ የ25 በመቶ ቀረጥ ዛሬ ተግባራዊ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ዛሬ የሚጀምረው እና በቻይና ምርቶች ላይ የጣለችውን ቀደም ሲል 10 በመቶ የነበረውን ተጨማሪ ቀረጥ በእጥፍ አሳድጋው 20 በመቶ ማስገባቷ ታውቋል።

ትረምፕ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚፈልሱትን ሕገ-ወጥ ስደተኞች እና ድንበር ተሻግሮ የሚጓጓዘውን ሕገ ወጥ እና አደገኛ መድሃኒት ዝውውር እንዲያግዱ የጠየቋቸው ሁለቱ የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ጎረቤቶች ሜክሲኮ እና ካናዳ የተባለውን ማድረጋቸውን ይፋ ካደረጉም በኋላ አዲሱን ቀረጥ ጥለውባቸዋል።

ትረምፕ በትላንትናው ዕለት ይህንኑ ማስታወቃቸውን ተከትሎም ሦስቱ የዩናይትድ ስቴትስ ዋና ዋና የአክሲዮን ገበያዎች ከፍተኛ ውድቀት ሲያስመዘግቡ፤ ዛሬ ማለዳ በአክሲዮን ገበያዎቹ መክፈቻ ላይም እያንዳንዳችው በ2 በመቶ አዘቅዝቀው ታይተዋል።

ከሦስቱ ሀገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ በጣሉት ከፍተኛ የቀረጥ ጭማሪ የተነሳ አሜሪካውያን ሸማቾች እና የንግድ ድርጅቶች አንዳንድ ጊዜያዊ የኢኮኖሚ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል’ ያሉት ትረምፕ "ነገር ግን በሦስቱ አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች የቀረጥ ክፍያውን ለማስቀረት ሲሉ ፋብሪካዎቻቸው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለማዘዋወር ይገደዳሉ" ሲሉ ተናግረል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትረምፕ ለወሰዱት የቀረጥ ጭማሪ አገራቸው አፀፋ እንደምትሰጥ የተናገሩት የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ "ይህ ፍትሃዊነት የጎደለው እርምጃ በዋዛ አይታለፍም”ብለዋል። አክለውም አገራቸው 107 ቢሊዮን ዶላር በሚገመቱ የአሜሪካ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ የምትጥል መሆኗን ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG