ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በሦሪያ ተፈጸመ የተባለውን ኬሚካዊ የጦር መሣሪያ ጥቃት አስመልክቶ በዛሬው የትዊተር መልዕክታቸው “ዩናይትድ ስቴትስ በሦሪያ ላይ ጥቃት የምትከፍትበትን ቀን ፈፅሞ አልተናገርኩም” ብለዋል።
“ጥቃቱ ፈጥኖም፣ ዘግይቶም ሊካሄድ ይችላል” ይላል የትዊተር መልዕክታቸው።
ይህንኑ አስመልክቶ የፈረንሣዩ መሪ ኢማኑኤል ማክሮን ዛሬ ሲናገሩ ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ ኬሚካዊ የጦር መሣሪይ ለመጠቀማቸው ፈረንሣይ ማረጋገጫ አላት ብለዋል። ለዚህም ባመቻት ቀን ምላሹን ትሰጣለች ሲሉ ደማስቆን አስጠንቅቀዋል።
የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርክል በበኩላቸው ኬሚካዊ የጦር መሣሪያን መጠቀም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለማሳየት የሚወሰድ ዕርምጃን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። ሀገራቸው በየትኛውም ዓይነት ወታደራዊ እርምጃ እንደማትሳተፍ ግን ቻንስለር አንጌላ መርክል አስረድተዋል።
በዋሺንግተን ባለሥልጣናትና ተንታኞችም በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራ ጣምራ ወታደራዊ ምላሽ በቀናት ውስጥ ሊሰጥ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ