በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ አንዳንድ ስደተኞች ከፌደራል መንግሥቱ የሚያገኙትን ጥቅማ-ጥቅም ለማስቆም የታለመ ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ


ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጀንዋሪ 20 ቀን 2025 ዓ.ም በዋይት ሃውስ ኦቫል ኦፊስ የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ሲፈርሙ።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጀንዋሪ 20 ቀን 2025 ዓ.ም በዋይት ሃውስ ኦቫል ኦፊስ የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ሲፈርሙ።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለገቡ ስደተኞች የፌዴራል መንግሥቱ የሚሰጠውን ድጋፍ ለማስቆም የታለመ ፕሬዝደንታዊ ትእዛዝ መፈረማቸውን ዋይት ሃውስ ትላንት አስታወቀ። ይሄም ፕሬዝደንቱ በሀገሪቱ ኢምግሬሽን ጉዳይ ላይ ከወሰዷቸው ጥብቅ ርምጃዎች አንዱ ነው።

ዋይት ሀውስ ጨምሮ እንዳመለከተው፣ ትዕዛዙ "በግብር ከፋይ አሜሪካውያን ወጭ የሚረዱ ማናቸውም ለሕገ-ወጥ የውጭ ዜጎች የሚሰጡ ጥቅማ-ጥቅሞች" ለማስቆም የታለመ ነው። ይሁን እንጂ ውሳኔው የትኞቹን ጥቅማጥቅሞች ኢላማ እንዳደረገ መግለጫው ግልጽ አላደረገም። አሁን በሥራ ላይ ባሉት ሕጎች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የገቡ የውጭ ዜጎች ከድንገተኛ ህክምና በስተቀር ለስደተኞች የሚሰጡትን ጥቅሞች አያገኙም።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1982 የጸደቀው የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ፤ የወላጆቻቸው የኢሚግሬሽን ይዞታ ምንም ይሁን ምን ለልጆች በአጠቃላይ ከ1ኛ እስከ 12ተኛ ክፍል ትምሕርት የመከታተል መብት ያጎናጽፋል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1996 የተደነገገው የሕግ ማሻሻያ በአንጻሩ በሕገ-ወጥ መንገድ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች መንግሥት ለስደተኞች የሚፈቅዳቸውን ጥቅማ-ጥቅሞች እንደሚከለክል ያስታወሰው የዋይት ሃውስ መግለጫ፤ “ሕጉ የሚያዘው አሠራር ቀስ በቀስ ተፋልሷል” ብሏል። አክሎም “ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በተለይ የቀድሞው አስተዳደር የሕጉን ዓላማዎች የሚያሰናክሉ ርምጃዎች በተደጋጋሚ ወስዷል። በዚህም የግብር ከፋዩ ሕዝብ ሃብት ያለአግባብ ወጪ እንዲሆን አድርጓል" ሲል ትተችቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG