በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሪፐብሊካን ፓርቲው ጉባኤ ዛሬ ይከፈታል


የሪፐብሊካን ፓርቲው ጉባኤ የሚካሄድበት አዳራሽ ሚልዋኪ ከተማ ዊስከንስን ክፍለ ሀገር
የሪፐብሊካን ፓርቲው ጉባኤ የሚካሄድበት አዳራሽ ሚልዋኪ ከተማ ዊስከንስን ክፍለ ሀገር

የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ ዛሬ ሰኞ ይከፈታል፡፡ ትረምፕ በዚሁ ሳምንት የፓርቲያቸው ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ሆነው በይፋ ለመሰየም ተዘጋጅተዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ቅዳሜ የቀድሞው ፕሬዚደንት በፔንሲልቬኒያ ክፍለ ግዛት በትለር ከተማ ላይ ለደጋፊዎች ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ ጥይት ተኩሶ ሊገድላቸው ስለሞከረው አጥቂ የፌዴራል መንግሥቱ ባለስልጣናት ምርመራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዊስከንስን ክፍለ ሀገር ሚልዋኪ ከተማ ውስጥ ለሚካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲው ጉባኤ የጸጥታ ጥበቃ ብርቱ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ሆኖም የፌዴራል መንግሥቱ የሕግ አስከባሪ ባለስልጣናት ቀደም ብሎ የተሰናዱበትን ስፋት ያለው የጸጥታ ጥበቃ እቅድ የመቀየር ሃሳብ እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡

ለሚልዋኪው ጉባኤ የተመደቡት የዩናይትድ ስቴትስ የምስጢራዊ የደሕንነት አገልግሎት አስተባባሪ ኦድሪ ጊብሰን ሲቺኖ ትላንት እሁድ በቴሌቭዢን በተላለፈ ገለጻቸው “ለጉባኤው ባዘጋጀነው የጸጥታ አጠባበቅ ዕቅድ እንተማመናለን፡፡ ሌላ ምንም ዓይነት ለውጥ ለማድረግ አናስብም” ብለዋል፡፡

ትረምፕ ከዋሽንግተን ኤግዛሚነር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የፊታችን ሐሙስ የጉባኤው ንግግራቸው “በፕሬዚደንት ጆ ባይደን ፖሊሲዎች የበረታ ትኩረት የሚሰጥ" እንደሚሆን ጠቁመው “ሆኖም አሁን የብሔራዊ አንድነት ጥሪም የተካተተበት ንግግር ይሆናል” ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ትላንት እሁድ ባደረጉት ንግግር በቀድሞው ፕሬዚደንት ላይ የተፈጸመው ጥቃት እንደሀገር ሁላችንም የቆምንለትን በሙሉ የሚጻረር ነው፡፡ እንደ ሀገር አንደአሜሪካዊ እኛ የምንገለጽበት አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ድርጊት ልንፈቅድ አይገባም” ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ በቀድሞው ፕሬዚደንት ትረምፕ ጥይት ተኩሶ የግድያ ሙከራ ያደረገው ተጠርጣሪ ቶማስ ማቲው ክሩክስ የተባለ የሃያ ዓመት ወጣት መሆኑን ገልጿል፡፡ ጥቃቱን ለማድረስ ያነሳሳው ምክንያት ግን አሁንም እንዳልታወቀ አመልክቷል፡፡

በቀጣይም ሚስጥራዊ የመሪዎች ደህንነት ጥበቃ አገልግሎቱ የሚስተር ትረምፕን ደህንነት አስፈላጊ የሆነው አቅም በሙሉ ተጠቅሞ ይጠብቃል ሲሉ ባይደን ቃል ገብተዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG